ቀጥታ፡

በክልሉ ለመሰረተ ልማት ዝርጋታና ለዘመናዊ ግብርና ትኩረት ተሰጥቷል

 

አዳማ፤ የካቲት 6/2018(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል ለመሰረተ ልማት ዝርጋታና ለዘመናዊ ግብርና ትኩረት መሰጠቱን የክልሉ የሥራ ሃላፊዎች ገለጹ።

የጨፌ ኦሮሚያ 6ኛ የሥራ ዘመን 5ኛ ዓመት 10ኛ መደበኛ ጉባኤ በአዳማ ገልማ ጨፌ እየተካሄደ ነው።

የጨፌ አባላት በፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ የቀረበውን የክልሉ መንግስት የስድስት ወራት ሥራ አፈጻጻም ሪፖርት መነሻ በማድረግ ተጨማሪ ማብራሪያ ጠይቀዋል።

አባላቱ የመሰረተ ልማት ለማሟላት እየተደረገ ያለውን ጥረት በጥንካሬ የሚነሳ ቢሆንም በአንዳንድ አካበቢዎች ቀሪ ሥራዎች አሉ ብለዋል።

የአገልግሎት መቆራረጥና የመሰረተ ልማት ያልደረሰባቸው አካባቢዎች ላይ የበለጠ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

በአንዳንድ አካበቢዎች የሚስተዋለው የፕሮጀክቶች በጊዜ አለመጠናቀቅና የጥራት ጉድለትም ሊፈተሽ እንደሚገባ አመልክተዋል።

የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተጀመሩ ተግባራት የበለጠ ሊጠናከሩ እንደሚገባ ነው አባለቱ ያነሱት።

ከአባለቱ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የክልሉ መንገዶችና ሎጂስቲክስ ቢሮ ሀላፊ ኢንጀነር ሄለን ታምሩ ከመንገድ መሰረተ ልማት ጋር ለተያያዙ ችግሮችን እልባት ለመስጠት አፋጣኝ እርምጃ እየተወሰደ ነው ብለዋል።

ባለፉት ስድስት ወራት በተለያዩ ምክንያቶች የዘገዩ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ክፍት ማድረግ መቻሉን አንስተዋል።

የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ሀላፊ ጌቱ ገመቹ በበኩላቸው፣ በክልሉ የግብርና ግብዓቶችን በብቃት በማሰራጨት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተሰሩ ሥራዎች ተጨባጭ ውጤት አስመዝግበዋል ነው ያሉት።

የተገኘውን ስኬት የበለጠ ለማላቅ የግብርና ሜካናይዜሽንና የቴክኖሎጂ አቅርቦትን በሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ የማድረጉ ተግባር ይቀጥላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም