ኢትዮጵያ ታላላቅ ኹነቶችን ለማስተናገድ የፈጠረችው አቅምና ውጤታማነት እየታየ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ታላላቅ ኹነቶችን ለማስተናገድ የፈጠረችው አቅምና ውጤታማነት እየታየ ነው
አዲስ አበባ፤የካቲት 7/2018 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ ታላላቅ ዓለም አቀፋዊና አህጉራዊ ኹነቶችን ለማስተናገድ የፈጠረችው አቅምና ውጤታማነት በተግባር እየታየ መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ ገለጹ።
39ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ "ዘላቂ የውኃ አቅርቦትና ደኅንነቱ የተጠበቀ የንጽህና አጠባበቅ ሥርዓቶችን ማረጋገጥ፤ ለአጀንዳ 2063 ግቦች ስኬታማነት” በሚል መሪ ሀሳብ ዛሬ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ የጉባዔው መክፈቻ መርሃ ግብር እንደተጠናቀቀ በሰጡት መግለጫ፤ ኢትዮጵያ ትናንት ሁለተኛውን የጣሊያን-አፍሪካ ስብሰባ በስኬት በማስተናገድ ዛሬ ደግሞ 39ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔን በስኬት እያስተናገደች ትገኛለች ብለዋል።
በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደው ሁለተኛው የጣሊያን አፍሪካ ጉባዔ በስኬት መጠናቀቁን ገልጸው፤ ጉባዔው በአዲስ አበባ መካሄዱ የመዲናዋን የዲፕሎማሲ ማዕከልነት ማሳያ መሆኑን አንስተዋል።
ጉባዔው በአፍሪካና ጣሊያን መካከል ያሉ ግንኙነቶችን ስትራቴጂክ በሆነ መንገድ ወደ አጋርነት ማሳደግ የሚያስችሉ አቅጣጫዎች የተቀመጡበት መሆኑንም ተናግረዋል።
በጉባዔው ስድስት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ውይይት መደረጉን ጠቅሰው፤ ከእነዚህም መካከል የጤና ጉዳይ አንዱና ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ እየሰራች ያለችውን ተግባር ማጠናከር የሚያስችል ነው ብለዋል።
በትምህርትና ስልጠናም ኢትዮጵያ ትምህርት ለትውልድ በሚል ከቅድመ መደበኛ ጀምሮ በትኩረት እየሰራችበት ያለ ዘርፍ መሆኑን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ከተለያዩ አማራጮች ንጹህ ኢነርጂ ለማመንጨት እየሰራች መሆኑን ያስታወሱት ሚኒስትር ዴኤታው፤ የጣሊያን ትብብር ታዳሽ ኃይል ለማምረት የሚደረገውን ጥረት የበለጠ እንደሚያጠናክረው ተናግረዋል።
ግብርናና ውሃም ውይይት የተደረገባቸው ጉዳዮች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
39ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ በመሪ ሀሳብ መሰረት ውሃ ለልማትና እድገት አቅጣጫዎች ወሳኝ መሆኑን አመልክተው፤ ኢትዮጵያ ያላትን የውሃ ሀብት በውጤታማነትና በመርህ ላይ ተመስርታ ለመጠቀም ያላትን ዝግጁነት የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጉባዔው ላይ ኢትዮጵያ ፍትሃዊ የውሃ ተጠቃሚነትና የባህር በር ለማግኘት የምታደርገውን ጥረትና እያከናወነች ያለውን የልማት ስራዎች መግለፃቸውን አንስተዋል።
መድረኩ ኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፍ እያከናወነቻቸው ያሉ ተግባራትን ለማስተዋወቅ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ ከበርካታ ባለድርሻ አካላት ጋር የተለያዩ የሁለትዮሽ ውይይቶችን መደረጋቸውን አንስተው፤ ኢትዮጵያ ከተለያዩ ሀገራት ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የምታጠናክርበት መሆኑን ገልፀዋል።
በርካታ መሪዎች ጉባዔውን ለመታደም ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውን ጠቅሰው፤ ይህም ኢትዮጵያ ትላልቅ ኹነቶችን ለማስተናገድ የፈጠረችውን አቅምና ውጤታማነቷን ማሳያ ነው ብለዋል።