የገቢ አሰባሰብን በማዘመን የህዝቡን ሁለንተናዊ የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ የተቋማት የተቀናጀ ጥረት ወሳኝ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የገቢ አሰባሰብን በማዘመን የህዝቡን ሁለንተናዊ የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ የተቋማት የተቀናጀ ጥረት ወሳኝ ነው
ባህር ዳር ፤ የካቲት 7/2018 (ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል የገቢ አሰባሰቡን በማዘመን የህዝቡን የመሰረተ-ልማትና የማሕበራዊ አገልግሎት ጥያቄ ለመመለስ የተቋማት የተቀናጀ ጥረት ወሳኝ መሆኑን የክልሉ ምክትል ርዕሰ-መስተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር) ገለጹ።
የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ከገቢዎች ሚኒስቴር የባህር ዳር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ጋር በመተባበር ለገቢ አሰባሰብ የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ተቋማትና ነጋዴዎች በባህር ዳር ከተማ የዕውቅና መርሃ ግብር አካሂዷል።
በመድረኩ ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር)፤ በክልሉ ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ በተገቢው መልኩ በመሰብሰብ የልማት ስራዎችን ለማከናወን የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
የገቢ አሰባሰቡን ፈጣንና ቀልጣፋ ለማድረግም ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች እየተተገበሩ መሆኑንና በዚህም ተጨባጭ ውጤት መምጣቱን ተናግረዋል።
በመሆኑም የህዝቡን የመሰረተ-ልማትና የማሕበራዊ አገልግሎት ጥያቄ ለመመለስ የተቋማት የተቀናጀ ጥረት ወሳኝ መሆኑን አጽዕኖት ሰጥተዋል።
የተገኙ ለውጦችን አጠናክሮ ለማስቀጠል ታማኝ ግብር ከፋዮችን ማበረታታት እንዳለ ሆኖ የግብር ስወራን ለመከላከል ጥብቅ አሰራርን በመከተል ወንጀለኞችን የህግ ተጠያቂ የማድረግ ስራም ትኩረት ተሰጥቶታል ብለዋል።
የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ሃላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የገቢ አሰባሰቡ የዲጂታል አሰራርን እየተከተለ በመሆኑና ቀልጣፋ አሰራር በመዘርጋቱ የገቢ መሰብሰብ አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት 100 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ በስድስት ወራት 50 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ መቻሉን ጠቅሰው በተለይም የኤሌክትሮኒክስ ታክስ አስተዳደር (ኢ-ታክስ) ለገቢው መጨመር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል ብለዋል።
በገቢዎች ሚኒስቴር የባህር ዳር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ ካሳሁን ደመመ፤ የክልሉን የገቢ አቅም በአግባቡ ለመሰብሰብ የተቀናጀ አሰራር አስፈላጊ መሆኑን አንስተው በዚህም የተጀመረው ጥረት አበረታች መሆኑን ተናግረዋል።
በመድረኩ ለግብር አሰባሰቡ የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ተቋማት፣ ነጋዴዎችና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ዕውቅና ተሰጥቷል።