ቀጥታ፡

ጣሊያን  በአጀንዳ 2063 የተያዙ ግቦች እንዲሳኩ የምታደርገውን ትብብር አጠናክራ ትቀጥላለች 

አዲስ አበባ፤ የካቲት 7/2018 (ኢዜአ)፡-ጣሊያን በአጀንዳ 2063 የተያዙ ግቦች እንዲሳኩ የምታደርገውን ትብብር አጠናክራ እንደምትቀጥል የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ ገለፁ።  

39ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ "ዘላቂ የውኃ አቅርቦትና ደኅንነቱ የተጠበቀ የንጽህና አጠባበቅ ሥርዓቶችን ማረጋገጥ፤ ለአጀንዳ 2063 ግቦች ስኬታማነት” በሚል መሪ ሀሳብ ዛሬ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።

የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር፤ ጣሊያን በ39ኛው የአፍሪካ ህብረት ጉባዔ ላይ እንድትሳተፍ ላገኘችው ታሪካዊ እድል ምስጋና አቅርበዋል።


 

የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ የአህጉሪቷን መሰረታዊ የፖለቲካ አማራጮችና ስትራቴጂካዊ አቅጣጫዎች የሚወሰንበት ነው ብለዋል።

የጣሊያን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በትብብር ላይ የተመሰረተ መሆኑን አንስተው፤ እውነተኛ ትብብር በእኩልነት ላይ የተመሰረተ፣ ሁለቱም ወገኖች ለጋራ ግብ ተቀናጅተው የሚሰሩበት ግንኙነት መሆኑን ገልፀዋል።

ጣልያን በእኩልነት ላይ የተመሰረተ እውነተኛ ትብብርን እንደምትፈልግ ገልጸው፤ ትናንት በአፍሪካ ምድር ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ የተካሄደውን ሁለተኛውን የጣልያን-አፍሪካ ጉባዔም ለማሳያነት አንስተዋል ።

ለጉባዔው መሳካት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) እና ለአፍሪካ ህብረት መሪዎች ምስጋና አቅርበዋል።


 

በጉባዔው ጣልያን በልዩ ልዩ የአፍሪካ ሀገራት በመሠረተ ልማት፣ ግብርና፣ ጤናና ስልጠና ላይ እየተገበረችው ያለችው የማቴይ እቅድ የበለጠ ለማጠናከር የሚያስችል ውይይት መደረጉን ገልፀዋል።

የማቴይ እቅድ የጣሊያን ብቻ ሳይሆን አፍሪካ የያዘችውን አጀንዳ 2063 ዕቅድ በተለይም የዘንድሮውን መሪ ሃሳብ ለማሳካት የሚያስችሉ ፕሮጀክቶች በጋር ቅንጅት የሚተገበርበት መሆኑንም ተናግረዋል።

ዕቅዱ በአጀንዳ 2063 የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት ያለንን  እውቀት፣ ቴክኖሎጂ እና ኢንቨስትመንት ለአገልግሎት የምናውልበት መድረክና በአፍሪካ አህጉር አቀፍ ነፃ የንግድ ቀጣና የተያዘውን የተባበረችና የበለፀገች አፍሪካ የመፍጠር ትልም የሚያሳካ ነው ብለዋል። 

አፍሪካውያን ወጣቶች ከስደት ይልቅ በሀገራቸው ሰርተው እንዲለወጡ የሰውን ኃይል ልማትና የትምህርት ጥራትን ማሻሻል የሚያስችሉ ስራዎችን ማከናወን እንደሚገባ ገልፀዋል።

ለዚህም በክህሎት ልማት ላይ ኢንቨስት ማድረግ እንዲሁም የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ በትብብር መስራት ያስፈልጋል ብለዋል። 

ጣልያን ከአፍሪካ ሕብረት ጋር በመተባበር በእነዚህ ተግባራት ላይ አበክራ እየሰራች መሆኑንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም