የአኅጉሩ ትልቁ ሀብት የተፈጥሮ ጸጋ ብቻ ሳይሆን ጠንካራ ተቋማትን የመገንባት ፈጠራን የማሳደግ እና ለዘላቂ ልማት ያለው አስተዳደራዊ ችሎታ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአኅጉሩ ትልቁ ሀብት የተፈጥሮ ጸጋ ብቻ ሳይሆን ጠንካራ ተቋማትን የመገንባት ፈጠራን የማሳደግ እና ለዘላቂ ልማት ያለው አስተዳደራዊ ችሎታ ነው
አዲስ አበባ፤ የካቲት 7/2018 (ኢዜአ)፡- የአኅጉሩ ትልቁ ሀብት የተፈጥሮ ጸጋ ብቻ ሳይሆን፣ ጠንካራ ተቋማትን የመገንባት፣ ፈጠራን የማሳደግ እና ለዘላቂ ልማት ያለው አስተዳደራዊ ችሎታ መሆኑን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
39ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ "ዘላቂ የውሃ አቅርቦትና ደህንነቱ የተጠበቀ የንጽህና አጠባበቅ ስርዓቶችን ማረጋገጥ፥ ለአጀንዳ 2063 ግቦች ስኬታማነት” በሚል መሪ ሀሳብ መካሄድ ጀምሯል።
በጉባኤው መክፈቻ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ባደረጉት ንግግር የአፍሪካ እና የዓለም አቀፍ መሪዎችን ወደ ኢትዮጵያ እንኳን በደኅና መጣችሁ በማለት፣ የአፍሪካን ታሪካዊ ዐሻራ እና ጽኑ ርዕይ አፅንዖት ሰጥተው ገልጸዋል።
የአኅጉሩ ትልቁ ሀብት የተፈጥሮ ጸጋ ብቻ ሳይሆን፣ ጠንካራ ተቋማትን የመገንባት፣ ፈጠራን የማሳደግ እና ለዘላቂ ልማት ያለው አስተዳደራዊ ችሎታ መሆኑን አሳስበዋል።
በውኃ ልማት፣ በኢነርጂ፣ በምግብ ዋስትና እና በኢንዱስትሪ ልማት ረገድ እየታዩ ያሉ መሻሻሎችን በማንሳት፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ፣ በስንዴ ምርት ራስን የመቻል ጥረትን እና እየተስፋፉ ያሉ የኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንቶችን ለአፍሪካዊ መፍትሔዎች እና ለጋራ ብልጽግና ማሳያ ተጨባጭ ምሳሌዎች አድርገው ጠቅሰዋል።
አኅጉሩ የደረሰበት ጠንካራ የዕድገት ጉዞ፣ የኢትዮጵያን የ10.2% ተጠባቂ ዕድገት፣ እንዲሁም የአኅጉሩን የስነ-ሕዝብ ብልጫ ለመጠቀም በወጣቶች፣ በጤና እና በትምህርት ላይ ኢንቨስት ማድረግ ያለውን አስፈላጊነት ገልጸዋል።
በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር አማካኝነት የሚታየውን የአየር ንብረት መሪነት፣ በ"ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030" ሥር እየተከናወነ ያለውን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን፣ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ የታዩ ስኬቶችን እና የአኅጉራዊ ትስስር መስፋፋትን አጉልተዋል።
በመጨረሻም ዓለም አቀፋዊ አጀንዳዎችን የመቅረጽ አቅም ያለው እና ለሁሉም አፍሪካውያን የሚተርፍ፤ ልማትን፣ ዕድልን እና ክብርን የሚያረጋግጥ በራሱ የሚተማመንና የተባበረ የአፍሪካ ሕብረት እንዲኖር ጥሪ አቅርበዋል።