በአፍሪካ የንጹህ መጠጥ ውሃና የንጽህና አጠባበቅ ሥርዓትን ለማረጋገጥ የተቀናጀ ስርዓት ማጠናከር ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በአፍሪካ የንጹህ መጠጥ ውሃና የንጽህና አጠባበቅ ሥርዓትን ለማረጋገጥ የተቀናጀ ስርዓት ማጠናከር ይገባል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 7/2018 (ኢዜአ)፡-በአፍሪካ የንጹህ መጠጥ ውሃና የንጽህና አጠባበቅ ሥርዓትን ለማረጋገጥ የተቀናጀ አሠራርን ማጠናከር እንደሚገባ የአንጎላ ፕሬዝዳንት ዦአዎ ሎሬንዞ ገለጹ፡፡
39ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ "ዘላቂ የውኃ አቅርቦትና ደኅንነቱ የተጠበቀ የንጽህና አጠባበቅ ሥርዓቶችን ማረጋገጥ፤ ለአጀንዳ 2063 ግቦች ስኬታማነት” በሚል መሪ ሀሳብ ዛሬ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
በዚሁ ወቅት ቡሩንዲ የ2026 የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበርነትን ከአንጎላ በይፋ ተረክባለች።
ተሰናባቹ የሕብረቱ ሊቀ-መንበርና የአንጎላ ፕሬዝዳንት ዦአዎ ሎሬንዞ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር፤ አፍሪካ እ.ኤ.አ በ2026 ትልቅ ግብ በማስቀመጥ ወደ ትግበራ መግባቷን ተናግረዋል፡፡
ይህም ዘላቂ የውሃ አቅርቦትንና ደህንነቱ የተጠበቀ የንጽህና አጠባበቅ ሥርዓቶችን ማረጋገጥ መሆኑን ገልጸው፤ ይህ ለአጀንዳ 2063 ስኬት ወሳኝ መሆኑን አስታውቀዋል።
ንፁህ የመጠጥ ውሃና የንጽህና ሥርዓት ማግኘት ግዴታ ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ ይህም ከመንግስታት ባለፈ የኩባንያዎችና የሲቪክ ማህበራትን የተቀናጀ ጥረት እንደሚጠይቅ አጽንኦት ሰጥተዋል።
የቡሩንዲ ፕሬዝዳንት ኤቫሪስቴ ንዳይሽሚዬ አዲስ የኅብረቱ ሊቀመንበር ሆነው መመረጣቸውም አህጉሪቱ በውሳኔ አሰጣጣቸውና በጥበባቸው ላይ ያላትን እምነት የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል።
አዲሱ ሊቀመንበር አፍሪካን ከተጋረጠባት የኋላቀርነት አዙሪት ለማውጣትና የተነደፉ ፕሮግራሞችን በንቃት ለማስፈጸም ትልቅ ኃላፊነት እንደሚጠብቃቸው ጠቁመዋል።
ፕሬዝዳንት ሎሬንዞ በስልጣን ዘመናቸው አብረዋቸው ለሰሩት ለአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር፣ ለቴክኒክ ባለሙያዎችና ለመላው ቡድን ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
አፍሪካን ወደ ላቀ የብልጽግና አድማስ ለማሸጋገር የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉና ሁሉም አባል ሀገራት ለአዲሱ የወቅቱ ሊቀመንበር ስኬት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።