ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አስተማማኝ የባህር በር ባለቤት መሆን ለቀጣናው ዘላቂ መረጋጋትና ብልፅግና ወሳኝ ነው

አዲስ አበባ፤ የካቲት 7/2018 (ኢዜአ)፡- አፍሪካን ከዓለም እያስተሳሰረች ያለችው ኢትዮጵያ አስተማማኝ የባህር በር ባለቤት መሆን ዘላቂ  ዕድገትን፣ ቀጣናዊ መረጋጋትና ብልፅግናን ለማረጋገጥ መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።

39ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በጉባኤው መክፈቻ ባደረጉት ንግግር፥ ሀገራችን በኢትዮጵያ አየር መንገድ በኩል አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ትስስርን እያጠናከረች ትገኛለች ብለዋል። 

በዚህም ሕዝቦችን እያገናኘን፣ ገበያዎችን እያስተሳሰርን፣ እንዲሁም የሸቀጦችን ጉዞ እያቀላጠፍን ነው ብለዋል።

ይህንን ግስጋሴ ለማስቀጠልም፣ ኢትዮጵያ አፍሪካን በዓለም አቀፍ የእሴት ሰንሰለት ትልቅ ስፍራ እንዲኖራት የሚያደርግና በአህጉሪቱ ግዙፉን አውሮፕላን ማረፊያ እየገነባች መሆኗን ጠቅሰዋል።

ይህ ግዙፍ  አውሮፕላን ማረፊያ የመጪው ትውልድ መግቢያ በር እንደሚሆንም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ከአቪዬሽን ሚናዋ ባለፈ፣ በኢትዮ ቴሌኮም በኩል አህጉራዊ ስትራቴጂካዊ አጋርነትን በማጠናከር በመላ አፍሪካ የዲጂታል ተደራሽነትን እያስፋፋች እንደምትገኝ አንስተዋል።

ሆኖም ግን፣ ትስስር የተሟላ መሆን አለበት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ለሚገኝባት ኢትዮጵያ ዘላቂ ዕድገትን ለማረጋገጥ  ብዝኃ አማራጭ ያለው ተደራሽነት ያስፈልጋታል ብለዋል።

በመሆኑም በሰላማዊ የትብብር መርህ አስተማማኝ የባህር በር መዳረሻ እንዲኖራት ማድረግ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤት መሆንም ለአፍሪካ ቀንድ የኢኮኖሚ እጣ ፈንታ፣ ዘላቂ የጋራ መረጋጋትና ብልፅግና መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑን በአፅንኦት ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም