ኢትዮጵያ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ዩኒቨርሲቲ ለማቋቋም በዝግጅት ላይ ትገኛለች - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ዩኒቨርሲቲ ለማቋቋም በዝግጅት ላይ ትገኛለች - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ የካቲት 7/2018 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) ዘርፍ ያላትን ልምድ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ዩኒቨርሲቲ ለማቋቋም በዝግጅት ላይ መሆኗን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ "ዘላቂ የውሃ አቅርቦትና ደህንነቱ የተጠበቀ የንጽህና አጠባበቅ ስርዓቶችን ማረጋገጥ፤ ለአጀንዳ 2063 ግቦች ስኬታማነት” በሚል መሪ ቃል በሕብረቱ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
በመክፈቻው መርሃ ግብር ላይ ንግግር ያደረጉት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ የኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ ሽግግር ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 በሚል ስትራቴጂ እየተመራ መሆኑን ገልጸዋል።
ዜጎችን ማዕከል ያደረገ የዲጂታል መሠረተ ልማት እየተገነባ መሆኑን ጠቅሰው፤ በተለይም ፋይዳ የተሰኘው ብሔራዊ የዲጂታል መታወቂያ ከክፍያ ሥርዓቶችና ከመረጃ ልውውጥ አውታሮች ጋር በመቀናጀቱ ዜጎች ቀልጣፋና ደህንነቱ የተጠበቀ አገልግሎት እንዲያገኙ እያስቻለ መሆኑን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2020 በአፍሪካ ቀዳሚ የሆነውን የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ማቋቋሟን አስታውሰዋል፡፡
በአሁኑ ወቅትም ኢትዮጵያ በመደመር ፍልስፍና ላይ የተመሠረተና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) ዩኒቨርሲቲ ለመክፈት ዝግጅት ላይ መሆኗን ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲው የሰውን ልጅ እሴቶች ከማሽን ኢንተለጀንስ ጋር የሚያስተሳስር፣ አካባቢያዊ ሁኔታዎችን ከዓለም አቀፍ ሳይንሳዊ ምርምር ጋር የሚያቀናጅ እንዲሁም አፍሪካ በቴክኖሎጂው ዘመን የራሷን አዎንታዊ አሻራ እንድታሳርፍ የሚያስችል እንደሚሆንም አብራርተዋል።
ይህ የቴክኖሎጂ ሽግግር የአገልግሎት አሰጣጥን ከማዘመን ባለፈ፣ የኢኮኖሚ ዕድገትን በማፋጠን አፍሪካ በዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ መድረክ ያላትን ተሳትፎ እንደሚያጠናክር ጠቅላይ ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል፡፡