ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ከቀጣናው ባለፈ ለአፍሪካ ሀገራት የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ የአፍሪካን የጋራ ብልፅግና ለማረጋገጥ እየሰራች ነው

አዲስ አበባ፤ የካቲት 7/2018 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ ከቀጣናው ባለፈ ለአፍሪካ ሀገራት የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ የአፍሪካን የጋራ ብልጽግናን ለማረጋገጥ እየሰራች መሆኑን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡  

39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ "ዘላቂ የውሃ አቅርቦትና ደህንነቱ የተጠበቀ የንጽህና አጠባበቅ ስርዓቶችን ማረጋገጥ፤ ለአጀንዳ 2063 ግቦች ስኬታማነት” በሚል መሪ ቃል በሕብረቱ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።

በመክፈቻው መርሃ ግብር ላይ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባደረጉት ንግግር፤ እንግዶችን ወደ ጥንታዊቷና የሰው ልጅ መገኛ ወደ ሆነችው ኢትዮጵያ እንኳን ደህና መጣችሁ ብለዋል፡፡


 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው ውሃ ከሀብትነት ባለፈ የልማት፣ የፈጠራ እና የመረጋጋት መሠረት መሆኑን ገልጸዋል፡፡  

የአፍሪካ የውሃ ራዕይ 2025ን መሠረት በማድረግ ኢትዮጵያ በኃላፊነት ላይ የተመሰረተ የውሃ አጠቃቀም ለልማት ያለውን ፋይዳ በተግባር እያሳየች መሆኑን ገልጸዋል። 

ለዚህም የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለቤት ውስጥና ለኢንዱስትሪ ኃይል ማመንጫነት ከመዋሉም ባለፈ፣ ለጎረቤት ሀገራት የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ የአፍሪካን የጋራ ብልጽግና የሚያረጋግጥ የብልሃት ውጤት መሆኑን ጠቅሰዋል።

የአፍሪካ ኢኮኖሚ ከእስያ ጋር እኩል በሚባል ደረጃ እያደገ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ኢትዮጵያ በበጀት ዓመቱ መጨረሻ 10 ነጥብ 2 በመቶ ዕድገት እንደምታስመዘግብ ጠቁመዋል። 

እ.ኤ.አ በ2035 አፍሪካ ከዓለም በበለጠ ወጣት የሰው ኃይል የምታበረክት መሆኗን ገልጸው፣ ይህንንም ወደ ብልፅግና ለመቀየር በትምህርት፣ በጤና እና በተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት ላይ ኢንቨስት እያደረጉ መሆኑን አብራርተዋል።

የአፍሪካ ከተሞች አረንጓዴ፣ ለሰው ልጅ ምቹ እና የወጣቶችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ መሆን እንዳለባቸው ጠቁመው፣ በአዲስ አበባ የተከናወኑ የወንዝ ዳርቻ ልማቶች ለዚህ ምሳሌ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ የተከናወነው የወንዝ ዳርቻ ልማት የተበከሉ የውሃ መስመሮችን ወደ ንፁህና ደማቅ የሕዝብ መዝናኛ ስፍራዎች መቀየሩን ተናግረዋል፡፡

ይህም የጎርፍ አደጋን ከመቀነሱ ባለፈ ክብርን በመመለስ ማህበራዊ ትስስር እንዲጠናከር ማድረጉን ተናግረዋል፡፡


 

የወደፊቱ የአፍሪካ ከተማ በእግር ለመጓዝ ምቹ፣ አረንጓዴ፣ ወጣቶችን ማዕከል ያደረገ፣ እንዲሁም ክብርና ባለቤትነት የሚሰማበት መሆን እንዳለበትም ተናግረዋል፡፡

በገጠር አካባቢዎችም ዘመናዊ አሰራር የዜጎችን ኑሮ እያሻሻለና ማህበረሰቡን ከገበያ ጋር እያገናኘ ይገኛል ብለዋል፡፡ 

ይህ የተቀናጀ አካሄድ ልማትን ከአካባቢ ጥበቃና ከአየር ንብረት እንክብካቤ ጋር ያስተሳስራል ሲሉም ገልጸዋል፡፡ 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እስካሁን ከ48 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን መትከሏን አስታውቀዋል።  

የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ በፍትሃዊነት ሊታይ እንደሚገባ ጠቅሰው፤ አፍሪካም በዓለም አቀፍ መድረክ በአንድ ድምጽ መናገር እንዳለባት አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም