ኢትዮጵያ በምግብ ዋስትናና በሕፃናት ሥርዓተ-ምግብ ያስመዘገበቻቸው ስኬቶች ለአፍሪካ ሀገራት ትልቅ ተሞክሮ የሚሆኑ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በምግብ ዋስትናና በሕፃናት ሥርዓተ-ምግብ ያስመዘገበቻቸው ስኬቶች ለአፍሪካ ሀገራት ትልቅ ተሞክሮ የሚሆኑ ናቸው
አዲስ አበባ፤ የካቲት 7/2018 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ በምግብ ዋስትናና በሕፃናት ሥርዓተ-ምግብ ያስመዘገበቻቸው ስኬቶች ለአፍሪካ ሀገራት ትልቅ ተሞክሮ የሚሆኑ ናቸው ሲሉ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ ገለጹ፡፡
የሌሶቶ ንጉሥና የአፍሪካ ሕብረት የሥርዓተ-ምግብ አምባሳደር ንጉሥ ሌትሲዬ ሣልሳዊ በተገኙበት በአፍሪካ የሕፃናት ዕድገትና የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት ላይ ያተኮረ ከፍተኛ የመሪዎች ውይይት ተካሂዷል፡፡
በመድረኩ ላይ የተሳተፉት በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ፤ ኢትዮጵያ የተቀናጀ አሰራርን በመከተል በርካታ ውጤቶች አስመዝግባለች ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ የሕፃናትን ጤናማ ዕድገትና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እየተገበረቻቸው ያሉ የሰቆጣ ቃል ኪዳን፣ የሌማት ትሩፋትና የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብሮች ከፍተኛ ስኬት እያመጡ መሆኑን ገልጸዋል።
የሰቆጣ ቃል ኪዳን የሕፃናትን የመቀንጨር ችግርን ለመቅረፍና ጤናማ ዕድገትን ለማፋጠን በተከናወኑ ተግባራት በሚሊዮን የሚቆጠሩ እናቶችና ሕፃናት ተጠቃሚ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
የሌማት ትሩፋትና የአረንጓዴ ዐሻራ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ፣ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የግብርና ሥርዓት ለመገንባት የተከናወኑት ተግባራት ለውጥ እያመጡ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
መንግሥት የተመጣጠነ የምግብ አቅርቦትን በአስተማማኝ ደረጃ ለማረጋገጥ የጀመራቸውን ጥረቶች አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
የሀገር በቀል ፋይናንስ የሥርዓተ-ምግብ ስራዎችን በዘላቂነት ለመደገፍ የሀገር ውስጥ የገንዘብ አቅምን ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸው፤ የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋሙ ተግባራትን በመፈፀም የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል፡፡
የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦትን ለማረጋገጥ በጋራ በመሥራት ለአፍሪካ ብልፅግና መሠረት የሆነውን የሰው ኃይል ማልማት እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡
የቀድሞው የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የአዳም ፋውንዴሽን የቦርድ ሊቀ መንበር ደመቀ መኮንን በበኩላቸው፤ በተመጣጠነ የምግብ እጥረት ሳቢያ በርካታ የአፍሪካ ህፃናት ተጎጂ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በአፍሪካ ከ59 ሚሊዮን በላይ ህፃናት በመቀንጨር አደጋ ተጋላጭ ናቸው ያሉት አቶ ደመቀ፤ ለዚህም የአፍሪካ ሀገራትና የልማት አጋሮች በቁርጠኝነት ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።
የአፍሪካ የወደፊት ዕጣ ፈንታና የአጀንዳ 2063 ስኬት በእናቶችና ሕፃናት ጤናና ክብር ላይ የተመሰረተ መሆኑንም አስገንዝበዋል።