ቀጥታ፡

በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀልን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ኢትዮጵያ በትጋት እየሠራች ነው

አዲስ አበባ፤ የካቲት 6/2018 (ኢዜአ)፡- በሰዎች የመነገድና በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገርን ጨምሮ ሌሎች ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከል ኢትዮጵያ በከፍተኛ ቁርጠኝነት እየሠራች መሆኗን የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ተወካይ ታምራት ሙሉጌታ (ዶ/ር) ተናገሩ።


 

ታምራት ሙሉጌታ (ዶ/ር) ይህን የተናገሩት በሰዎች መነገድ እና በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀል ምርመራ ሥልጠና የማጠቃለያ መርሐ-ግብር ላይ ነው።

ዩኒቨርሲቲው ከዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት፣ ከፈረንሳይ የውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር የቴክኒክ ትብብር ኦፕሬተር፣ ከጀርመን የልማት ተራድዖ ዓለም አቀፍ ድርጅት፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ለሕግ አስከባሪ አካላት ሥልጠና በመስጠት ተገቢውን ክኅሎት እና ዕውቀት እያስጨበጠ መሆኑም ገልጸዋል።


 

በሲቪፖል የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ቢሮ አስተባባሪ እና ቡድን መሪ ማርኮ ቡፎ በበኩላቸው፤ ከተለያዩ ሀገራት ለተውጣጡ ኤጀንሲዎች ተወካዮች የተሰጠው ሥልጠና በተግባር ልምምድ ላይ ያተኮረ መሆኑን ጠቁመዋል።

ሠልጣኞቹ ለተጎጂዎች ተገቢውን ጥበቃ በማድረግ እና መረጃና ማስረጃ የሚያገኙበትን የሰላም ሞዴል ቃለ መጠይቅ በመጠቀም ፍትሕን ማስፈን እንደሚችሉ በሥልጠናው አረጋግጠናል ብለዋል። 

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በሰዎች የመነገድ እና በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀል ምርመራ የሥልጠና ልኅቀት ማዕከል በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና የምርመራ ዕውቀት ሽግግር ላይ የሚሠራ ተቋም መሆኑን የገለጹት ደግሞ በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ የውጭና የሠላም ማስከበር መምሪያ ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ጎሳዬ ታደሠ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም