የማቴይ ፕላን ከኢትዮጵያ የቅድሚያ ትኩረቶች ጋር የተቆራኘ ነው- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የማቴይ ፕላን ከኢትዮጵያ የቅድሚያ ትኩረቶች ጋር የተቆራኘ ነው- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ ፤የካቲት 6/2018 (ኢዜአ)፡- የማቴይ ፕላን (The Mattei Plan) የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርምን ጨምሮ ከኢትዮጵያ የቅድሚያ የትኩረት መስኮች ጋር የተቆራኘ ስትራቴጂካዊ ማዕቀፍ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ሁለተኛው የጣሊያን-አፍሪካ ጉባዔ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል እየተካሄደ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጉባኤው በአፍሪካ እና አውሮፓ ወሳኝ የትብብር ምዕራፍ ወቅት የሚካሄድ መሆኑን ገልጸዋል።
ቃል ወደ ተግባር እና ሀሳቦችን ወደ ግልጽ ውጤቶች በመቀየር ዜጎቻችን ተጠቃሚ ማድረግ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
ጣልያን በአፍሪካ እና በአውሮፓ መካከል ድልድይ ለመሆን እየሰራች እንደምትገኝ አመልክተዋል።
በማቴይ እቅድ አማካኝነት (Mattei Plan) የኢነርጂ ደህንነት፣ ዘላቂ ልማት፣ የፍልሰት አስተዳደር እና የሰው ሀብት ልማት በማቀናጀት አጋርነት እና የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረተ ባደረገ መልኩ እየተተገበረ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ የዚህ ራዕይ አካል በመሆኗ ኩራት ይሰማታል ብለዋል።
ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ2024 በተካሄደው የመጀመሪያው የአፍሪካ-ጣልያን ጉባኤ ተሳትፎ ማድረጓን አውስተው ከዛ ጊዜ አንስቶ የቀጠለው ትብብር ኢትዮጵያ ከቃላት ባለፈ በተግባር ያላትን ቁርጠኝነት ያሳየችበት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ከጣልያን እና ከአፍሪካውያን ወንድሞች እና እህቶች እንዲሁም አጋሮች ጋር በመሆን ስትራቴጂካዊ ምክክርን የዜጎችን ኑሮ ወደሚቀይር የልማት ውጤት ለማሻገር በቁርጠኝነት ትሰራለች ብለዋል።
ኢትዮጵያ አፍሪካን ከተቀረው ዓለም ጋር እያስተሳሰረች ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአህጉሪቷ የዲፕሎማሲ ማዕከል መሆኗን ገልጸዋል።
በሎጅስቲክስ እና አቪዬሽን ተመራጭነቷ እያደገ መምጣቱን ጠቅሰው፥ በርካታ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶች እያስተናገደች እንደምትገኝ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ቀጣናዎችን፣ ገበያዎች እና ሀሳቦችን እንዲተሳሰሩ እንዲሁም የአፍሪካ ድምጽ በዓለም መድረክ እንዲሰማ እያደረገች ነው ብለዋል።
የኛ ትልቁ ሀብት ህዝባችን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ አፍሪካ ወጣት ህዝብ ያላት፣ ለመፍጠር እና ለመምራት ዝግጁት መሆኗን አመልክተዋል።
በወጣት እና በክህሎት ላይ መዋዕለ ንዋይን ማፍሰስ የስራ እድል በመፍጠር እና አቅምን በመጠቀም የዛሬን ችግሮችን መፍታት እና ለነገ እድሎች መዘጋጀት እንደሚገባ ነው ያስነገነዘቡት።
ቴክኖሎጂ በተለይም የሰው ሰራሽ አስተውሎት ለመጻኢ ጊዜ ቁልፍ የሆነ ዘርፍ መሆኑን ጠቅሰው፥ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች፣ የኢነርጂ መሰረተ ልማትን ማዘመን፣ ስርዓተ ምግብን ማሻሻል፣ የጤና ስርዓትን መቀየር እና ንግድን በማሳለጥ ህዝብን ማዕከል ያደረጉ ስራዎችን ማከናወን እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
የአፍሪካን ትጉህ እና የመፍጠር አቅም ያለው ህዝብ ከአውሮፓ ልምድ፣ ቴክኖሎጂ እና ካፒታል ጋር በማስተሳሰር ብልጽግናን ለሁለቱ አህጉራት አልፎም ለተቀረው ዓለም ማምጣት ይቻላል ነው ያሉት።
የማቴይ እቅድ ከኢትዮጵያ የቅድሚያ ትኩረቶች ጋር የተጣጣሙ መሆናቸውን ገልጸው፥ የሀገር በቀል ሪፎርም አጀንዳን እንደሚደግፍ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ቀጣናዊ መሰረተ ልማት ትስስር እና ቴክኖሎጂን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች እያከናወነች ያለውን ስራ ለዘላቂ ልማት መሰረት የሚጥል እና ለአፍሪካውያን የጋራ እሴቶች አስተዋጽኦ የሚያበረክት እንደሆነ ተናግረዋል።
የጣልያን እና አፍሪካ አጋርነት ትብብር ሚዛናዊ እና መጻኢ ጊዜን ያማከለ መሆኑን የሚያመላክት እንደሆነ አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ ከጣልያን እና አፍሪካ ጋር ያላትን ስትራቴጂካዊ አጋርነት ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸው፥ ፍትሃዊ እና የጋራ ብልጽግናን መሰረት ባደረገ መልኩ የአፍሪካ እና አውሮፓ ትብብርን እንቅረጽ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢዜአ የዲጂታል ሚዲያ ገጾች
https://linktr.ee/ENADigital