ኢትዮጵያ በጣሊያን-አፍሪካ ጉባኤ መሪ ተዋናይ በመሆኗ ኩራት ይሰማታል- የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በጣሊያን-አፍሪካ ጉባኤ መሪ ተዋናይ በመሆኗ ኩራት ይሰማታል- የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት
አዲስ አበባ፤ የካቲት 6/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የጋራ ርዕዮችን ወደ ተጨባጭ ተግባር ለመለወጥ በሚደረገው ሁለተኛው የጣሊያን-አፍሪካ ጉባኤ መሪ ተዋናይ በመሆኗ ኩራት እንደሚሰማት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።
ሁለተኛው የጣሊያን-አፍሪካ ጉባኤ በአዲስ አበባ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ጉባኤውን አስመልክቶ ባወጣው መረጃ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የጣሊያን አቻቸው ጆርጂያ ሜሎኒ ይህንን ታላቅ ስብሰባ በጋራ በማዘጋጀት በጣሊያን እና በአፍሪካ መካከል ያለውን አጋርነት ለማጠናከር ያላቸውን የጋራ ቁርጠኝነት በድጋሚ እያረጋገጡ እንደሚገኙ ገልጿል።
በአፍሪካ የዲፕሎማሲ መዲና አዲስ አበባ እየተካሄደ ያለው ይህ ጉባኤ፤ ዘላቂ ልማትን ለማምጣትና የአጀንዳ 2063 ግቦችን ለማፋጠን ኢትዮጵያ ያላትን የጋራ ጽኑ ፍላጎት የሚያጎላ መሆኑን አመልክቷል።
በተጨማሪም በጣሊያኑ የ"ማቲ ዕቅድ" (Mattei Plan) ሥር የተጀመረውን የላቀ ትብብር፤ እርስ በርስ መከባበር፣ የጋራ ብልጽግና እና ዘላቂ አጋርነት መርሆች ላይ ይበልጥ እንደሚያጠናክር ገልጿል።
መሪዎችን በማሰባሰብ፣ በንግድ፣ በኢነርጂ፣ በመሠረተ ልማት፣ በግብርና፣ በትምህርት እና በፈጠራ ዘርፎች ያሉንን የጋራ ርዕዮች ወደ ተጨባጭ ተግባር ለመለወጥ በሚደረገው በዚህ ውይይት መድረክ ኢትዮጵያ መሪ ተዋናይ በመሆኗ ኩራት እንደሚሰማት ጽሕፈት ቤቱ አስታውቋል።