የሕጻናትን ሁለንተናዊ ጤንነት የሚያረጋግጥ የሥርዓተ ምግብ ደኅንነት ቁርጠኛ እርምጃ ሊወሰድ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የሕጻናትን ሁለንተናዊ ጤንነት የሚያረጋግጥ የሥርዓተ ምግብ ደኅንነት ቁርጠኛ እርምጃ ሊወሰድ ይገባል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 6/2018 (ኢዜአ)፡- የአፍሪካ ሀገራት የሕጻናትን ሁለንተናዊ ጤንነት የሚያረጋግጥ የሥርዓተ ምግብ ደኅንነት ቁርጠኛ እርምጃ ሊወስዱ እንደሚገባ በአፍሪካ ሕብረት የጤና፣ ሰብዓዊ ጉዳዮችና የማኅበራዊ ልማት ኮሚሽነር አምባሳደር አማ ትውም አሞን አስገነዘቡ።
"አፍሪካ የተመጣጠነ ምግብ እጥረትን መከላከል ላይ በሚደረግ ስትራቴጂካዊ ኢንቨስትመንት ለሕጻናት ኅልውና ያላትን ቁርጠኝነት እንደገና ማደስ" በሚል መሪ ሐሳብ የ39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ ከፍተኛ የጎንዮሽ መድረክ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
ኮሚሽነር አምባሳደር አማ ትውም አሞን በዚሁ ወቅት፤ የአፍሪካ አጀንዳ 2063 እና የወደፊት ዕጣ ፈንታ የሚለካው በሕጻናቷ ጤና፣ አመጋገብና ክብር ላይ መሆኑን በአጽንኦት ገልጸዋል።
የአፍሪካ ሀገራት የተመጣጠነ ምግብ እጥረት መከላከል ላይ ስትራቴጂካዊ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ ለሕፃናት ሁለንተናዊ ደኅንነት በትኩረት ሊሠሩ እንደሚገባም ጥሪ አቅርበዋል።
የአንድ ሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት በጤናማ እናትና በሕጻናት ጤናማ የአስተዳደግ ሥርዓት ላይ የሚወሰን መሆኑን አስረድተዋል።
በዚህም የአፍሪካ ሀገራት የእናቶችና ሕጻናትን ሁለንተናዊ ደኅንነት ለማረጋገጥ በፖሊሲ፣ በበጀትና በተጠያቂነት የሚመራ ቁርጠኛ እርምጃ ሊወስዱ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ስለዚህ የአፍሪካን የኢኮኖሚ ዕድገትና ብልጽግና ለማረጋገጥ በእናቶችና ሕጻናት ላይ የሚደረግ ኢንቨስትመንትን ማሳደግ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የቀድሞው የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የአዳም ፋውንዴሽን የቦርድ ሊቀ መንበር ደመቀ መኮንን በበኩላቸው፤ በተመጣጠነ የምግብ እጥረት ሳቢያ በርካታ የአፍሪካ ሕጻናት ተጎጂ እየሆኑ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
በአፍሪካ ከ59 ሚሊየን በላይ ሕጻናት ለመቀንጨር አደጋ ተጋላጭ መሆናቸውን ገልጸው፤ ለዚህም የአፍሪካ ሀገራትና የልማት አጋሮች በቁርጠኝነት ሊሠሩ ይገባል ብለዋል።