በአፍሪካ የዲጂታል መሰረተ ልማትን በማስፋፋት አፍሪካን ከዓለም ገበያ ጋር ለማስተሳሰር ትብብራችንን አጠናክረን እንቀጥላለን-ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ - ኢዜአ አማርኛ
በአፍሪካ የዲጂታል መሰረተ ልማትን በማስፋፋት አፍሪካን ከዓለም ገበያ ጋር ለማስተሳሰር ትብብራችንን አጠናክረን እንቀጥላለን-ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 6/2018(ኢዜአ)፦በአፍሪካ የዲጅታል መሰረተ ልማትን በማስፋፋት አፍሪካን ከዓለም ገበያ ጋር ለማስተሳሰር ትብብራችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ ገለጹ፡፡
ሁለተኛው የጣሊያን-አፍሪካ ስብሰባ በአዲስ ዓለም አቀፍ ስብሰባ ማዕከል መካሄድ ጀምሯል፡፡
ኢትዮጵያና ጣሊያን ሁለተኛውን የአፍሪካ ጣሊያን ጉባዔ በጋራ ያዘጋጁት ሲሆን፤ የሀገራችንን የዲፕሎማቲክ የስበት ማዕከልነቷን ዳግም የሚያረጋግጥ፣ በዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ያላትን ቦታ በጉልህ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚያሳይ ነው።
በመርሃ ግብሩ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ፣ የአንጎላ ፕሬዝዳንትና የወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር ጆአዎ ሎሬንዞ፣ የተመድ ዋና ጸሀፊ አቶኒዮ ጉቴሬዝ፣ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሀሙድ አሊ ዩሲፍ እና የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች ተገኝተዋል፡፡
የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ጣሊያንና አፍሪካ በተለያዩ መስኮች በትብብር እየሰሩ ነው፡፡
የጣሊያንና አፍሪካ የጋራ ግቦችን ለማሳካት በኢነርጂ፣በትምህርትና ስልጠና፣ በጤና በዲጂታልና በመሰረተ ልማት ግንባታ ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በታዳሽ ሀይል፣ በአረንጓዴ ልማት ሽግግር፣ በምግብ ዋስትና እና መሰል መስኮች ያለው ትብብር ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
በአፍሪካ የዲጂታል መሰረተ ልማትን በማስፋፋት አፍሪካን ከዓለም አቀፉ ግብይት ለማስተሳሰር በጋራ እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል፡፡
ጣሊያን በመንግስትና በግሉ ዘርፍ ትብብር በሀይል መሰረተ ልማት ላይ በትኩረት እየሰራች መሆኑን ገልጸው፤ ከአፍሪካ ጋር በትብብርና የጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ትብብራችን ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
በአፍሪካ ጠንካራ የጤና ስርዓት ለመገንባት የላቀ ትብብር አለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሯ፤ ትብብሩ ጠንካራና ተደራሽ የጤና ስርዓት መገንባት እንደሚያስችል ገልጸዋል፡፡
በኢንዱስትሪ ልማትና በግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ላይ በጋራ እየሰሩ መሆኑን ገልጸው፤ በወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ ላይ ልዩ ትኩረት ተደርጓል ብለዋል፡፡
በማቲ ፕላን መሰረት ሁሉም ፕሮጀክቶች ትምህርትና ስልጠና ላይ ያተኮሩ መሆናቸውን በማንሳት፤ ትኩረታቸው የአፍሪካን ህዝብ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ጣሊያን ለሰው ሃብት ልማት ትኩረት እንደምትሰጥ በማንሳት፤ ወጣቶች በአህጉራቸው ስራ ተፈጥሮላቸው ስደትን ማስቀረት ይገባል ብለዋል፡፡