በክልሉ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተከናወኑ ተግባራት የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ትልቅ እገዛ አድርገዋል--ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተከናወኑ ተግባራት የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ትልቅ እገዛ አድርገዋል--ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ
አርባ ምንጭ፤የካቲት 6/2018 (ኢዜአ)፡-በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተከናወኑ ተግባራት የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ትልቅ እገዛ ማድረጋቸውን ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ገለጹ።
በአርባ ምንጭ ከተማ እየተካሄደ ባለው የክልሉ ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ባቀረቡት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት የምክር ቤት አባላት ላነሱት ጥያቄ ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷል።
አባላቱ ከኑሮ ውድነት፣ ከሥራ አጥነት፣ ከጤና እና ከትምህርት አገልግሎት መስፋፋት እንዲሁም ከውሃና ሌሎች መሠረተ ልማት ዝርጋታ ጋር በተያያዘ የተለያዩ ጥያቄዎችን አንስተዋል።
ከምክር ቤት አባላቱ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ የሰጡት ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ ባለፉት ስድስት ወራት ህዝቡን ተጠቃሚ ያደረጉ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማቶች ተከናውኗል ብለዋል።
በተለይም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተከናወኑ ተግባራት የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ትልቅ እገዛ ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።
በበጀት ዓመቱ ቀሪ ጊዜያትም የበልግ፣ የመስኖ፣ የሌማት ትሩፋት ስራዎችን በተቀናጀ መንገድ በማከናወን የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ ይሰራል ብለዋል።
በግንባታ ላይ የሚገኙ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች እንዲሁም አዳዲስ የልማት ፕሮጀክቶችን ለማከናወን ከመንግስት በተጨማሪ የህዝቡ ተሳትፎ እንዲያድግ ይደረጋል ብለዋል።
እንደ አቶ ጥላሁን ገለጻ ከትምህርት ልማት አኳያ የተከናወኑ ሥራዎች የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን ለማሳደግ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።
በክልሉ በሂደት የነበሩ የተለያዩ የጤና ተቋማት ግንባታ ሥራዎችን በማጠናቀቅ የተሳለጠ የጤና አገልግሎት ለመስጠት የተጀመሩ ተግባራትም ይጠናከራሉ ብለዋል ።
ለህዝቡ የሚሰጡ የመንግስት አገልግሎቶችን ለማሳለጥ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎቶችን ለማስፋፋት በልዩ ሁኔታ ይሰራል ሲሉም ርዕሰ መስተዳድሩ አክለዋል።
የምክር ቤቱ አባላት የርዕሰ መስተዳድሩን ምላሽና ማብራሪያ ካዳመጡ በኋላ የ2018 በጀት ዓመት የስድስት ወራት አፈጻጸም ሪፖርትን በሙሉ ድምፅ አፅድቀዋል።
ምክር ቤቱ በነገው ዕለት የተለያዩ አዋጆችንና ሹመቶችን ያጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል።