በሲዳማ ክልል የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች የሚመልሱ ሥራዎች እንዲከናወኑ የድጋፍና ክትትል ሥራ ተከናውኗል-አፈ ጉባኤ ፋንታዬ ከበደ - ኢዜአ አማርኛ
በሲዳማ ክልል የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች የሚመልሱ ሥራዎች እንዲከናወኑ የድጋፍና ክትትል ሥራ ተከናውኗል-አፈ ጉባኤ ፋንታዬ ከበደ
ሀዋሳ፤ የካቲት 6/2018 (ኢዜአ)፡-በሲዳማ ክልል የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች የሚመልሱ ሥራዎች እንዲከናወኑ የድጋፍ እና ክትትል ሥራ መከናወኑን የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋንታዬ ከበደ ገለፁ።
የሲዳማ ክልል ምክር ቤት አባላት በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል፡፡
የምክር ቤቱ ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋንታዬ ከበደ በዚህ ወቅት እንደተናገሩት የክልሉ ህዝብ ሲያነሳቸው የነበሩ የልማት ጥያቄዎችን የሚመልሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራት እንዲከናወኑ ምክር ቤቱ ድርሻውን ሲወጣ ቆይቷል።
በመሰረተ ልማት ዝርጋታ በተለይም የኤሌክትሪክ፣ የውሃ፣ የመንገድ እንዲሁም በግብርና የመስኖ አውታሮችን በማስፋፋት አርሶ አደሩ ከዝናብ ጥገኝነት ተላቆ ዓመቱን ሙሉ አምርቶ ተጠቃሚ እንዲሆን የተሰሩ ሥራዎች ውጤታማ መሆናቸውን አንስተዋል።
በከተሞችም ኮሪደር ልማትን ጨምሮ በተከናወኑ የልማት ሥራዎች የከተሞችን ገፅታ ከመቀየር ባለፈ ህዝቡን በልማት ተጠቃሚ ያደረጉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑም ተናግረዋል፡፡
በሀዋሳ ከተማ በተለየ መንገድ እየተመራ ያለው የኮሪደር ልማት ሥራ ከተማዋን ይበልጥ ውብና ሳቢ የሚያደርጋት መሆኑን ጠቅሰው ልማቱ የሥራ ባህልን በመቀየር፣ የሥራ ዕድል በመፍጠር እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴን እያቀላጠፈ መሆኑን ተናግረዋል።
የተጀመሩ የልማት ስራዎች የበለጠ እንዲጠናከሩ ምክር ቤቱ የድጋፍ እና ክትትል ስራውን በተቀናጀ መልኩ ያከናውናል ብለዋል።
በጉብኝቱ ላይ ከተሳተፉ የምክር ቤቱ አባላት መካከል አቶ ዮሐንስ ተክሉ፣ በሀዋሳ ዙሪያ ወረዳ የተዘረጉ የመስኖ ፕሮጀክቶች አርሶ አደሩ እርሻውን በዘመናዊ መንገድ እንዲያከናወን ዕድል የሰጡ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
ምክር ቤቱ ሲነሱ የነበሩ የህዝብ ጥያቄዎች በተለይም በድልድይ ግንባታ እንዲሁም በከተሞች ልማትና ሌሎች ተግባራት እየተሰጡ ያሉ ምላሾች ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ሌላዋ የምክር ቤቱ አባል ወይዘሮ ኤልሳቤጥ ፊቼ በበኩላቸው በጉብኝቱ አርሶ አደሩ በዘመናዊ መንገድ አልምቶ ምርታማነቱን እንዲያሳድግ ብሎም ከግብርና ወደ ኢንዱሰትሪ እንዲሸጋገር በር የሚከፍቱ ሥራዎች እንደተከናወኑ መመልከታቸውን ጠቅሰዋል፡፡
የምክር ቤቱ አባላት በጉብኝታቸው በሀዋሳ ዙሪያ ወረዳ፣ በወንዶ ገነት ከተማና በሀዋሳ ከተማ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎችን የጎበኙ ሲሆን ዋና አፈ ጉባኤዋን ጨምሮ ከፍተኛ የክልሉ አመራሮችም ተገኝተዋል፡፡