ቀጥታ፡

በጎንደር ከተማ የአምራች ኢንዱስትሪውን ችግሮች በጥናት በመለየት መፍትሄ እየተሰጠ ነው

ጎንደር፤ የካቲት 6/2018 (ኢዜአ)፡- በጎንደር ከተማ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የተሰማሩ አልሚ ባለሀብቶች የሚገጥሟቸውን ችግሮች በጥናት በመለየት መፍትሄ እየተሰጠ መሆኑን  የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ተናገሩ። 

አስተዳደሩ በከተማው በኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ከተሰማሩ ባለሀብቶች ጋር የምክክር መድረክ አካሂዷል። 

ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ቻላቸው ዳኘው በመድረኩ ላይ እንደገለጹት የከተማ አስተዳደሩ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚስተዋሉ ማነቆዎችን በመፍታት ለባለሃብቱ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እየተሰራ ነው።     


 

በዘርፉ የብድር አቅርቦትና የገበያ ትስስር፣ የግንባታ ማስፋፊያ ቦታና ሌሎች ጥያቄዎችን ለመመለስ  ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። 

በዚህም አምራች ኢንዱስትሪዎች ወደ ማምረት እንዲሸጋገሩ  እየተደረገ መሆኑን  አመልክተዋል።፡

የተሰጣቸውን የኢንቨስትመንት ቦታ አጥረው ለረጅም ጊዜ ያስቀመጡ ባለሃብቶች በገቡት ውል መሰረት ወደ ስራ መግባት እንዳለባቸው ጠቁመው በማይገቡት ላይ እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል።

በምክትል ከንቲባ ማእረግ የከተማ አስተዳደሩ የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ሃላፊ አቶ ግርማይ ልጃለም በበኩላቸው በከተማው በተቋቋሙ አምስት የኢንዱሰትሪ መንደሮች እስካሁን የኢንቨስትመንት ፈቃድ የወሰዱ  ከ250 በላይ ፕሮጀክቶች መኖራቸውን አመልክተዋል፡፡

ከነዚህ ውስጥም 51 አምራች ኢንዱስትሪዎች ወደ ማምረት በመሸጋገር ከ2 ሺህ 500 በላይ ለሚሆኑ ወገኖች የስራ እድል መፍጠራቸውን ገልጸዋል፡፡

ቀሪዎቹ ደግሞ ግንባታቸውን  አጠናቀው ለማምረት ዝግጁ የሆኑ፣ ግንባታቸውን ያቋረጡና ወደ ግንባታ ያልገቡ መሆናቸውን በተካሄደው ጥናት መረጋገጡን አስረድተዋል።

በጥናት የተለዩ ችግሮችን ለመፍታት በተደረገው ጥረትም ለ16 ባለሀብቶች የማስፋፊያ ቦታ መሰጠቱንና ለ49 አምራች ኢንዱስትሪዎች ከ3 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር እንዲያገኙ መመቻቸቱን አመልክተዋል፡፡

በከተማው በኢንቨስትመንት ዘርፉ ከተሰማሩ ባለሀብቶች መካከል አቶ ጅብሪል ማሩ በሰጡት አስተያየት በከተማው   ባለው ሰላምና በተደረገላቸው ድጋፍ  የዱቄት ፋብሪካቸው ስራ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡

በኢንዱስትሪ መንደሩ ውስጥ የህንጻ ግንባታ በማጠናቀቅ አሁን ላይ በማሽን ተከላ ላይ እንደሚገኙ የገለፁት ደግሞ በፕላስቲክ ውጤቶች ማምረት ዘርፍ የተሰማሩት አቶ ግዛቸው ሙሉቀን ናቸው።

በምክክር መድረኩ ላይ የከተማ አስተዳደሩ አመራሮችን ጨምሮ በከተማው በአምስት የኢንዱስትሪ መንደሮች በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች የተሰማሩ  ባለሀብቶች ተሳትፈዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም