ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የአፍሪካና የዓለም ትስስር ማዕከል ሆናለች- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ የካቲት 6/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የአፍሪካና የዓለም ትስስር ማዕከል መሆኗን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

2ኛው የጣሊያን-አፍሪካ ጉባዔ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል መካሄድ ጀምሯል።

ኢትዮጵያና ጣሊያን በጋራ ያዘጋጁት ይህ ጉባኤ የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ ማዕከልነት ዳግም የሚያረጋግጥና በዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ መድረክ ያላትን ቦታ በጉልህ የሚያሳይ ነው።

በጉባኤው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባደረጉት ንግግር፣ ኢትዮጵያ ስትራቴጂካዊ ውይይቶችን ወደ ተጨባጭ የልማት ውጤቶች ለመቀየር እየሰራች መሆኑን አንስተዋል፡፡


 

ከጣሊያን፣ ከአፍሪካውያን ወንድምና እህቶቿ እንዲሁም ከሌሎች አጋሮች ጋር የልማት ትብብሯን አጠናክራ እንደምትቀጥልም አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያ አፍሪካን ከዓለም ጋር የሚያገናኝ የዲፕሎማሲ፣ የኢቪየሽን እና የሎጂስቲክስ ማዕከል መሆኗን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሀገሪቱ የአፍሪካን ድምፅ በዓለም አቀፍ መድረኮች ከፍ ለማድረግ እየሰራች መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ዘላቂ ልማትና ብልፅግና መሰረት እየጣለች መሆኗን ጠቅሰው፥ ይህ አርዓያነት ያለው ጉዞዋ በዓለም አቀፍ የትብብር መስክም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የአፍሪካ ትልቁ ሀብት ወጣቱ መሆኑን በመጥቀስ፣ በክህሎትና በፈጠራ ላይ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ የወደፊቱን ዕድሎች መጠቀም እንደሚገባም ጠቁመዋል።

በተለይም ሰው ሰራሽ አስተውሎት ለዲጂታል ሽግግር፣ ለኢነርጂ መሠረተ ልማት፣ ለምግብ ዋስትና እና ለጤና ሥርዓት መሻሻል ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፥ ለዚሁ መዘጋጀትና መተግበርም ያስፈልጋል ነው ያሉት።

የጣሊያኑ ማቲ ፕላን ከኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ጋር እንደሚጣጣም ገልጸዋል።

ይህም በተለይ በታዳሽ ኃይል፣ በዘመናዊ ግብርና፣ በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እና በሰው ሀብት ልማት ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአፍሪካን የፈጠራ አቅም ከአውሮፓ ቴክኖሎጂና ካፒታል ጋር በማጣመር ለሁለቱም አህጉራት ብልጽግናን የሚያመጡ መፍትሔዎችን መገንባት እንደሚቻልም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም