በኢትዮጵያ ስደተኞችንና ተቀባዩን ማህበረሰብ ተጠቃሚ የሚያደርግ የሥራ ዕድል ፈጠራ ምኅዳር ተመቻችቷል - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ስደተኞችንና ተቀባዩን ማህበረሰብ ተጠቃሚ የሚያደርግ የሥራ ዕድል ፈጠራ ምኅዳር ተመቻችቷል
አዲስ አበባ፤የካቲት 6/2018(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ ስደተኞችንና ተቀባዩን ማህበረሰብ ተጠቃሚ የሚያደርግ የሥራ ዕድል ፈጠራ ምኅዳር መመቻቸቱን የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ዲኤታ ዶ/ር ተሻለ በሬቻ (ዶ/ር )አስታወቁ።
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከጀርመን ልማት ባንክና ከኒራስ ጋር በመተባበር ባዘጋጀው የፈጠራ ፈንድ ውድድር አሸናፊ ከሆኑ 19 ኢንተርፕራይዞችና የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ጋር የውል ስምምነት ተፈራርሟል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተሻለ በሬቻ (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ፤ ስምምነቱ የዜጎችን አስተማማኝና ዘላቂ የሥራ ዕድል ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ትርጉም የሚሰጠው መሆኑን ገልጸዋል።
በሥራ ዕድል ፈጠራ ዘርፍ የሴቶችን፣ አካል ጉዳተኞችን፣ስደተኞችንና ልዩ ልዩ የማህበረሰብ ክፍሎችን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ውጤታማ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
የትብብር ስምምነቱም ስደተኞችንና ተቀባዩን ማህበረሰብ የሚያስተሳስር በክህሎት የበለጸገ የሥራ ዕድል ፈጠራ ምኅዳር ለመገንባት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው አንስተዋል።
የኢንተርፕራይዝ፣የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች የፈጠራ ውድድር አዳዲስ የፈጠራ ሃሳቦችን በማፍለቅ በክህሎት የበለጸጉ የሥራ ዕድል ከባቢዎችን ለማስፋት እንደሚረዳ አብራርተዋል።
ለአሸናፊ የኢንተርፕራይዞች፣ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ተወዳዳሪዎች የተበረከተው የገንዘብ ሽልማትም የፈጠራና ክህሎት ውድድርን ለማሳደግ እንደሚስችል አንስተዋል።
የጀርመን ኤምባሲ ተወካይ አንጃ ፓውልስ፤ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ስደተኞችን በመቀበል የምታስናግድበትን ሥርዓት አድንቀዋል።
ኢትዮጵያ የዜጎችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚነት ለማሻሻል በምታደርገው ጥረት የጀርመን መንግስት ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
የጀርመን ልማት ባንክ ተወካይ ዮናስ ዲላ፤ የፈጠራ ፈንድ ኢንተርፕራይዞች ውድድር ሀገር አቀፍ የክህሎት ልማት አቅምን ለማሻሻል ጉልህ ፋይዳ እንደሚኖረው ገልጸዋል።
የንፋስ ስልክ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን ሸለማ ንጉሡ፤ ስምምነቱ ክህሎት መር የኢንዱስትሪ ቅንጅት በመፍጠር ስድተኞችንና የተቀባዩን ማህበረሰብ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና አለው ብለዋል።
የንብ ማነብና ማር ምርት ዘርፍ ተወካይ ይልማ ታደሰ በበኩላቸው፣ የተሰጣቸው የዕውቅና ድጋፍ ለቀጣይ ሥራቸው ተጨማሪ አቅም እንደሚሆን ገልጸዋል።
የስደተኞችንና ተቀባዩን ማህበረሰብ የሥራ ዕድል ፈጠራ ፕሮጀክት ተወዳዳሪ ተቋማት ወደሥራ ሲገቡ በሺዎች የሚቀጠሩ ስደተኞችንና ተቀባዩን ማህበረሰብ ተጠቃሚነት እንደሚያሳድግ ይጠበቃል።