የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ 65ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን በተለያዩ ዝግጅቶች ያከብራል - ኢዜአ አማርኛ
የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ 65ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን በተለያዩ ዝግጅቶች ያከብራል
ሀዋሳ ፤የካቲት 6/2018 (ኢዜአ)፡-በሀገር መከላከያ ሠራዊት የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ 65ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ከነገ የካቲት 7 እስከ 15 ድረስ በተለያዩ ዝግጅቶች ያከብራል።
የዕዙን የምስረታ በዓል አከባበር በማስመልከት ዛሬ መግለጫ የተሰጠ ሲሆን በዓሉ በነገው እለት በሀዋሳ ከተማ የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር በማካሄድ መከበር እንደሚጀምር ተመላክቷል።
ከተመሰረተ 65 ዓመታት ዕድሜ ያስቆጠረው የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ ከፍተኛ ጀግንነትን የፈጸሙ ኮማንዶ፣ አየር ወለድና ልዩ የጸረ ሽብር ሀይሎችን ሲያሰለጥን ቆይቷል።
እነዚህን የሀገር ባለውለታዎች ያፈራው የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ የመስረታ በዓሉን ምክንያት በማድረግ ነገ በሀዋሳ ከተማ ከማለዳው 12:00 ሰዓት ጀምሮ በወንዶችና በሴቶች ታዋቂ አትሌቶችን ጨምሮ ከሀዋሳና ከአጎራባች ከተሞች የተውጣጡ ከ10 ሺህ በላይ ሰዎች የሚሳተፉበት የሩጫ ውድድር እንደሚካሄድ ታውቋል።
በሩጫ ውድድሩ ላይ ለመሳተፍም አትሌቶች ወደ ሀዋሳ ከተማ መግባታቸውን በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ኢንተርናሽናል ኮርስ ሜጀረር ተሾመ በቀለ ገልጸዋል።
በዚህ ውድድር 202 ወንድና 80 ሴት ታዋቂ አትሌቶች እንደሚሳተፉ ገልጸው በአማራ፣ ኦሮሚያና ሲዳማ ክልሎች እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከሚገኙ ክለቦች እና በግል የሚወዳደሩ አትሌቶች ይሳተፋሉ ብለዋል።
በውድድሩ በሁለቱም ጾታ ከአንደኛ እስከ አምስተኛ ለሚወጡ አትሌቶች እንደየደረጃቸው የገንዘብ ሽልማት እንደሚሰጥም አመልክተዋል።
ውድድሩ መነሻና መድረሻውን ሀዋሳ ሱሙዳ አደባባይ ማድረጉንም ተጠቁሟል።
የሲዳማ ክልል መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሀላፊ አቶ ወሰንየለህ ስምኦን በበኩላቸው የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ 65ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በድምቀት እንዲከበር ክልሉ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅቶች አድርጓል ብለዋል።
መላው የሲዳማ ህዝብና የሀዋሳ ከተማ ነዋሪዎች የበዓሉ ታዳሚዎችን በእንግዳ ተቀባይነት ባህል ተቀብሎ ሊያስተናግድ እንደሚገባም አቶ ወሰንየለህ አሳስበዋል።