የአፍሪካ አገራት መሪዎች ለ39ኛው የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ አዲስ አበባ እየገቡ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ አገራት መሪዎች ለ39ኛው የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ አዲስ አበባ እየገቡ ነው
አዲስ አበባ፤የካቲት 6/2018(ኢዜአ)፦በአዲስ አበባ በሚካሄደው 39ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ የተለያዩ የአፍሪካ አገራት መሪዎች ወደ አዲስ አበባ እየገቡ ይገኛሉ።
የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ፣ የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ ፣ የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዚዳንት ሳልቫኪር ማያርዲት፣ የዛምቢያው ፕሬዚዳንት ሐካይንዴ ሒቺሊማ፣ የሊቢያ ፕሬዝዳንታዊ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሞሐመድ የኑስ ማንፊ (ዶ/ር) ለሕብረቱ ጉባኤ አዲስ አበባ ገብተዋል።
የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ አዲስ አበባ ሲደርሱ የማዕድን ሚኒስትር ኢንጅነር ሐብታሙ ተገኝ አቀባበል አድርገውላቸዋል።
የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ የገቢዎች ሚኒስትር ዓይናለም ንጉሴ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ አቀባበል አድርገውላቸዋል።
የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዚዳንት ሳልቫኪር ማያርዲትን የማዕድን ሚኒስትር ኢንጅነር ሐብታሙ ተገኝ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርሃኑ ጸጋዬ አቀባበል አድርገውላቸዋል።
የዛምቢያው ፕሬዚዳንት ሐካይንዴ ሒቺሊማ የማዕድን ሚኒስትር ኢንጅነር ሐብታሙ ተገኝ ተቀብለዋቸዋል።
የሊቢያ ፕሬዝዳንታዊ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሞሐመድ የኑስ ማንፊ (ዶ/ር) የሰላም ሚኒስትር አቶ መሐመድ እድሪስ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርሃኑ ጸጋዬ አቀባበል አድርገውላቸዋል።
39ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ "ዘላቂ የውሃ አቅርቦትና ደህንነቱ የተጠበቀ የንጽህና አጠባበቅ ስርዓቶችን ማረጋገጥ፤ ለአጀንዳ 2063 ግቦች ስኬታማነት” በሚል መሪ ሀሳብ ይካሄዳል።