ቀጥታ፡

የክልሉ መንግስት 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ዴሞክራሲያዊና ተዓማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በቁርጠኝነት እየሠራ ነው-ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ

አርባ ምንጭ ፤የካቲት 6/2018 (ኢዜአ) :- የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ፣ ተዓማኒና ተምሳሌታዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በቁርጠኝነት እየሠራ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ገለጹ።

የክልሉ ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤውን በአርባ ምንጭ ከተማ እያካሄደ ነው።


 

ለምክር ቤቱ የግማሽ በጀት ዓመት ሪፖርት ያቀረቡት አቶ ጥላሁን ከበደ እንዳሉት፤ በመጪው ግንቦት ወር ላይ የሚካሔደው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ፣ ተዓማኒና ተምሳሌታዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በቁርጠኝነት እየተሰራ ነው።

''በአንድ እጃችን የምርጫ ስራዎቻችንን በሌላኛው እጃችን ደግሞ ቀሪ የስድስት ወራት የልማትና የመልካም አስተዳደር አቅዶቻችንን ለማሳካት በቁርጠኝነት የምንሰራበት ነው'' ብለዋል።

ጠቅላላ ምርጫው ሰላማዊ፣ ፍትሐዊ እና ተዓማኒ እንዲሆንም በየደረጃው የተቀናጁ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሆነም ነው የገለጹት።

በዚሁ መሠረት የምክር ቤት አባላት ድርብ ኃላፊነት አለባቸው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ምርጫው ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባም አሳስበዋል።

የምክር ቤቱ አባላት ከምርጫ ስራው ጎን ለጎንም የክልሉን የዘንድሮው ዓመት ቀሪ እቅዶች ለመፈፀም የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ ማጠናከር እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

በተለይ የመቻቻልና የውይይት ባህልን በማስረጽ ሁሉም የምርጫ ተዋንያን ለምርጫ ህጉ ተገዥ መሆን እንደሚገባቸውም  አሳስበዋል።


 

ማህበረሰቡ ለሰላምና ለዴሞክራሲያዊ እሴቶች መነቃቃት በተለይ የጥላቻ ንግግሮችና የሀሰተኛ መረጃዎችን በወቅቱ በማረም ለምርጫው ሰላማዊነት የበኩሉን እንዲወጣ ነው ርዕሰ መስተዳድሩ ያመለከቱት።

ሰላማዊ ምርጫ የመንግስትና የምርጫ ቦርድ ስራ ብቻ ባለመሆኑ የሁሉም ተዋንያን የሞራል ግዴታ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ወጣቶችን ጨምሮ ሁሉም አካላት ለምርጫው ሰላማዊነት የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡም አስገንዝበዋል ።

ክልሉን የሰላም፣ የመቻቻልና የብልጽግና ተምሳሌት የማድረግ ራዕይ እውን እንዲሆን ከህዝብ ጋር በቅንጅት የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠላቸውንም ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቁመዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም