አምራችና ሸማቹን በቀጥታ በማገናኘት ገበያን የማረጋጋት ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
አምራችና ሸማቹን በቀጥታ በማገናኘት ገበያን የማረጋጋት ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል
ባህርዳር ፤የካቲት 6/2018 (ኢዜአ)፡-በአማራ ክልል አምራችና ሸማቹን በቀጥታ በማገናኘት ገበያ የማረጋጋት ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ ድረስ ሳህሉ(ዶ/ር) ገለጹ።
"የኢትዮጵያ ታምርት፤ እኛም እንሸምት"በሚል መሪ ሃሳብ አምራችና ሸማቹን በቀጥታ የሚያገናኝ ኤግዚቢሽንና ባዛር በባህር ዳር ተከፍቷል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ ክልሉ በኢንዱስትሪ፣ በኮንስትራክሽን፣ በግብርናና በአገልግሎት ዘርፎች እምቅ የመልማት ፀጋ አለው ብለዋል።
የክልሉ መንግስት ሰላምን ከማስከበር ጎን ለጎን ያለውን ጸጋ በማልማት የሕብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ሥራዎችን እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ባዛሩ አምራቹንና ሸማቹን በቀጥታ በማገናኘት ገበያውን ለማረጋጋት ወሳኝ ሚና እንዳለው ጠቅሰው፣ ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
የባህር ዳር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው በበኩላቸው ከተማዋን የቱሪዝም፣ የኢንዱስትሪና የኢንቨስትመንት መዳረሻ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ባለፉት ዓመታት የኢንዱስትሪ ዘርፉን ውጤታማነት ለማሳደግ በተደረገ ክትትልና ድጋፍ የኢንዱስትሪዎች ምርታማነት እያደገ መጥቷል ነው ያሉት።
በዘርፉ ለሚሰማሩ አዳዲስ ባለሃብቶችም አዳዲስ የኢንቨስትመንት ፍቃድ መሰጠቱን አመልክተዋል።
የባዛሩ መዘጋጀት ሕብረተሰቡ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ ዕድልን ይፈጥራል ብለዋል።
በባዛሩ ከተሳተፉት መካከል በንጽህና መጠበቂያ ምርት ላይ የተሰማሩት የዝና ሙሉቀን ባዛሩ ደንበኞቻቸውን በቀጥታ እንዲያገኙና የገበያ ትስስር እንዲፈጥሩ ማድረጉን ገልጸዋል።
ዛሬን ጨምሮ ለሶስት ቀናት በሚቆየው ኤግዚቪሽንና ባዛር ላይ ምግብና ምግብ ነክ፣ አልባሳት፣ የኮንስትራክሽንና ሌሎች የኢንዱስትሪና የግብርና ውጤቶች ቀርበዋል።