የበልግ እርሻን ቀድመው የሚጀምሩ አካባቢዎች በሚቀጥሉት አስር ቀናት የሚኖረውን የርጥበት ሁኔታ በአግባቡ ሊጠቀሙበት ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የበልግ እርሻን ቀድመው የሚጀምሩ አካባቢዎች በሚቀጥሉት አስር ቀናት የሚኖረውን የርጥበት ሁኔታ በአግባቡ ሊጠቀሙበት ይገባል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 6/2018(ኢዜአ)፦ የበልግ እርሻን ቀድመው የሚጀምሩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በሚቀጥሉት አሥር ቀናት የሚኖረውን የርጥበት ሁኔታ በአግባቡ እንዲጠቀሙበት ኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ገለጸ።
የኢትዮጵያ ሜቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ከየካቲት 4 እስከ የካቲት 13 ቀን 2018 ዓ.ም ባሉት አሥር ቀናት የሚኖረውን የአየር ሁኔታ ትንበያ ይፋ አደርጓል፡፡
ኢንስቲትዩቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ፣ የበልግ እርሻ እንቅስቃሴ ቀድመው የሚጀምሩ አካባቢዎች የሚገኘውን እርጥበት በአግባቡ እንዲጠቀሙበት አሳስቧል።
በሚቀጥሉት አሥር ቀናት በደቡብ ምዕራብ፣ በስምጥ ሸለቆና አዋሳኝ አካባቢዎች ላይ አነስተኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖር ገልጿል፡፡
በተጨማሪም በመካከለኛውና በደቡብ ምዕራብ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ የደመና ሽፋን እንደሚጨምር አመልክቷል፡፡
በጋምቤላ፣ በሰሜን ምዕራብ፣ በሰሜን ምስራቅና በደቡብ ምስራቅ አካባቢዎች የቀኑ ከፍተኛ የሙቀት መጠን ከ32 ዲግሪ ሴልሺየስ በላይ ሆኖ እንደሚቀጥል ተቋሙ ጠቁሟል።
በቀጣይ የሚኖረው የአየር ሁኔታ ለቋሚ ተክሎች የተሻለ እድገት እንዲያገኙ ያግዛል፣ ለአርብቶ አደሩ የግጦሽ ሳርና የመጠጥ ውሃ አቅርቦትን ለማሻሻል ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር እንዲሁም ለበልግ እርሻ ማሳን ቀድሞ ለማዘጋጀትና የአፈር ውስጥ እርጥበትን ለማሻሻል እንደሚረዳም ጠቅሷል፡፡
ሆኖም የእርጥበት መጠን ለሰብል ዝርያ የሚበቃ ባለመሆኑና ደረቅ አየር ሁኔታም ስለሚስተዋል አርሶ አደሩ ይህንን ተገንዝቦ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ኢንስቲትዩቱ አሳስቧል።
በሚቀጥሉት አሥር ቀናት በአብዛኞቹ ተፋሰሶች ላይ ደረቃማ የአየር ሁኔታ የሚጠበቅ በመሆኑ የገጸ-ምድር ውሃ ፍሰት ሊቀንስ እንደሚችል ተገልጿል።
በተለይም በባሮ አኮቦ፣ በኦሞ ጊቤ፣ በስምጥ ሸለቆና በገናሌ ዳዋ ተፋሰሶች ላይ ዝቅተኛ የውሃ ፍሰት እንደሚኖር የተገለጸ ሲሆን በውሃ አጠር አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎች ውሃን ከብክነትና ከብክለት እንዲከላከሉ፣ እንዲሁም አማራጭ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት መንገዶችን እንዲጠቀሙ ጥሪ ቀርቧል።
በሚቀጥሉት አሥር ቀናት ለበልግ እርሻ ዝግጅትና ለቋሚ ተክሎች እንክብካቤ አመቺ ቢሆኑም ለዝርያ የሚበቃ ዝናብ ባለመኖሩና የውሃ መጠን ሊቀንስ ስለሚችል አስፈላጊው ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ ተመላክቷል።