ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የአፍሪካን የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ ፈር ቀዳጅ ፕሮጀክት ነው - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የአፍሪካን የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ ፈር ቀዳጅ ፕሮጀክት ነው
አዲስ አበባ፤ የካቲት 6/2018(ኢዜአ)፦ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የአፍሪካን የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ ፈር ቀዳጅ አህጉራዊ ፕሮጀክት መሆኑን የውሃ ፖለቲካ ተመራማሪው ያዕቆብ አርሳኖ (ዶ/ር) ገለጹ።
ምሁሩ ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ ከግድቡ መጠናቀቅ ማግስት 39ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ የሚካሄድ መሆኑም ለጋራ አህጉራዊ ግቦች መሳካት የላቀ መነሳሳትን እንደሚፈጥር ተናግረዋል።
አፍሪካ ለረጅም ዘመናት በባርነትና በቅኝ ግዛት የቆየች አህጉር ናት ያሉት ያዕቆብ አርሳኖ(ዶ/ር)፥ አፍሪካውያን በፓን አፍሪካኒዝም ዕሳቤ አማካይነት ባደረጉት ትግል ከፖለቲካ ባርነትና ከቅኝ አገዛዝ ነፃ መውጣት ችለዋል ብለዋል።
ሆኖም ግን አህጉሪቱ ዛሬም ድረስ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ እየታገለች መሆኑን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ በልጆቿ ፅኑ አቋምና አቅም እንዲሁም በሀገር ውስጥ ሀብት የገነባችው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለአህጉራዊ የኢኮኖሚ ነፃነትን በማሳካት ረገድ እንደ ትልቅ አርዓያ የሚጠቀስ መሆኑን ዶክተር ያዕቆብ አስገንዝበዋል።
ግድቡ ከአፍሪካ ህብረት የ2063 አጀንዳ ግቦች ጋር ቀጥተኛ ትስስር ያለውና አፍሪካውያን የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው መወሰን እንደሚችሉ ያሳየ የፓን አፍሪካኒዝም መገለጫ መሆኑንም አክለዋል።
የሕዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ፈር ቀዳጅ የሆነ ታላቅ የልማት ፕሮጀክት ነው ብለዋል።
39ኛው የህብረቱ ጉባኤ ከግድቡ መጠናቀቅ ማግስት የሚካሄድ መሆኑም ለአፍሪካ መሪዎች ትልቅ የተነሳሽነት አቅም እንደሚፈጥር ገልፀዋል።
39ኛው የህብረቱ ጉባኤ በውሃ ላይ ያተኮረ መሆኑ፣ በአህጉሪቱ ያለውን የውሃ ሀብት ለልማት፣ ለዜጎች ጤና እና ለኑሮ መሻሻል ለመጠቀም ትኩረት ለመስጠት አስቻይ ሁኔታን ይፈጥራል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ በአካባቢ እና በውሃ ሀብት ጥበቃ ረገድ ያከናወነቻቸው ተግባራት በአርአያነት የሚጠቀሱ ናቸው ያሉት ዶክተር ያዕቆብ ለዚህም ስኬታማው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ዋነኛው ማሳያ ተደርጎ እንደሚወሰድ ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ግዙፍ የአየር ማረፊያ፣ የጋዝ እና የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታዎች መጀመራቸው ከኢኮኖሚ በዘለለ ስትራቴጂካዊ ፋይዳ እንዳላቸው አንስተዋል።
በመንግስት በኩል የተወሰደው ጠንካራ የስንዴ ልማት ስራ ኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነትን ከማረጋገጥ ባለፈ ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው መስክ ያላትን ተሰሚነት እንደሚያሳድገው አብራርተዋል።
ኢትዮጵያውያን በዓድዋ ጦርነት ያስመዘገቡት ድል የአፍሪካን የነጻነት ጎህ የፈነጠቀ መሆኑን በማንሳት፥ የዚህ ዘመን ትውልድ የልማት ድል የሆነው የሕዳሴ ግድብ ደግሞ የአፍሪካዊያን መፃዒ ዘመን የብስራት መልዕክት ነው ብለዋል።
ይህም አፍሪካዊያን በ21ኛው ክፍለ ዘመን በአንድነትና በትብብር መቆም ከቻሉ፣ የተሟላ ሉዓላዊነታቸውን በማረጋገጥ በዓለም መድረክ ከፍ የሚሉበት እድል ከፊታቸው እንዳለ አመላካች መሆኑን ጠቅሰዋል።