ቀጥታ፡

የዞኑ ተማሪዎች በዘንድሮው ሀገር አቀፍ ፈተና የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ዝግጅታቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል

ጊምቢ ፤ የካቲት 6/2018(ኢዜአ)፦ በዘንድሮው ሀገር አቀፍ ፈተና የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ዝግጅታቸውን አጠናክረው መቀጠላቸውን በምእራብ ወለጋ ዞን የሚገኙ ተማሪዎች አስታወቁ።

ኢዜአ በዞኑ ለሀገር አቀፍ ፈተናው እየተደረጉ ያሉ ዝግጅቶችን በማስመልከት የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችንና የትምህርት ቤት ርዕሰ መምህራንን አነጋግሯል።

በምእራብ ወለጋ ዞን ምቢ ከተማ አድቬንቲስት 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪ ሲፌኔት ሀምቢሳ እንደገለጸችው፤ በሀገር አቀፍ ፈተናው የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ጊዜዋን በአግባቡ በመጠቀም ጠንክራ እያጠናች ትገኛለች።


 

ለፈተናው የሚረዷትን  እና በበይነ መረብ አማካኝነት አጋዥ የሆኑ መጽሃፍትን በማንበብ ላይ እንደምትገኝ ገልፃ ለዚህም በመምህራኖች እገዛ እየተደረገላት መሆኑን ትናገራለች።

ባለፈው ዓመት በትምህርት ቤቱ የተመዘገበው የውጤት መሻሻል እሷን ጨምሮ የዘንድሮ ተፈታኝ ተማሪዎች ዘንድ በተነሳሽነት ስሜት እንዲተጉ እንዳደረጋቸው አውስታለች።

ሌላኛው የትምህርት ቤቱ የ12ኛ ክፍል ተማሪ ቀነኒ አብዮት እንደሚለው፤ የተሻለ ውጤት በማምጣት ዩኒቨርስቲ የመግባት ህልሙን ለማሳካት አጋዥ መጽሀፍቶችን እያነበበ እና ያለፉት አመታት የፈተና ጥያቄዎችንም በመከለስ ላይ ይገኛል።


 

አሁን ላይ በሀገር አቀፍ ፈተና የተሻለ ውጤት ለማምጣት በተናጥል ከሚያደርገው ዝግጅት በተጨማሪ  በቡድን  እየተዘጋጁ መሆኑንም ተናግሯል።

ተማሪ አበራ እጅጉ በበኩሉ፤ በፈተናው ውጤታማ ለመሆን ከመደበኛ የትምህርት ክፍለ ጊዜ በተጨማሪ የአዳር ጥናት በማካሄድ በትጋት እያሳለፈ መሆኑን ተናግሯል።


 

በዞኑ ዶንጎሮ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕስ መምህር  ዳንኤል ተሰማ፤ በ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በተደጋጋሚ ጊዜ የታየውን የውጤት ማሽቆልቆል ለመቀልበስ ከመደበኛ የትምህርት ክፍለ ጊዜ ወጪ አስፈላጊውን ድጋፍ ለተማሪዎቻቸው እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።


 

ተፈታኝ ተማሪዎች ጊዜያቸውን ለፈተናው የሚያግዛቸውን መጽሐፍቶች በማንበብ እንዲያሳልፉ እንዲሁም የተለያዩ ጥያቄዎች እንዲለማመዱ ከማድረግ ባለፈ በሥነ ልቦና ዝግጁ እንዲሆኑ በትምህርት ቤቱ መምህራን ያልተቋረጠ እገዛ እየተደረገ ነው ብለዋል። 

የአሮጂ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ሳመኤል ዋቅጋር እንዳሉት፣ በትምህርት ቤቱ በሀገር አቀፍ ፈተና ጥሩ ውጤት እንዲመዘገብ ለተማሪዎች አስፈላጊውን የመጽሐፍት አቅርቦት ከማሟላት ባሻገር፣ የትምህርት ክለሳ እየተሰጠ ነው።


 

ተማሪዎች ትርፍ ጊዜያቸውን በቤተመጽሐፍት ውሰጥ በጥናት እንዲያሳልፉ ድጋፍ እና ክትትል እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል። 

የተማሪዎችን  ውጤት ማሻሻል በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ውይይት ከትምህርት ቤቱ መምህራን ጋር መደረጉን ያነሱት ርእሰ መምህሩ ይህም ችግሩን በመለየት የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ አጋዥ እንደሚሆን ተናግረዋል።

የምእራብ ወለጋ ዞን የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አስተዳደር የሥራ ሂደት መሪ አቶ መኮንን አነጋረ  በበኩላቸው፤ የዞኑ ተማሪዎች በሀገር አቀፍ ፈተና የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ከመምህራን ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።


 

ለዚህም መምህራን ዓመቱን ሙሉ ተፈታኝ ተማሪዎችን ከሥነ-ልቦና ዝግጅት ጀምሮ የተለያዩ እገዛዎችን እንዲያደርጉላቸው አቅጣጫ ተቀምጦ ተግባራዊ እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በምእራብ ወለጋ ዞን 12 ሺህ 623 ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን እየተከታተሉ መሆናቸውንም አስታውቀዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም