የአፍሪካ ህብረት እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የባለብዙ ወገን አጀንዳዎች ላይ ያላቸውን አጋርነት ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆናቸውን ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ ህብረት እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የባለብዙ ወገን አጀንዳዎች ላይ ያላቸውን አጋርነት ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆናቸውን ገለጹ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 6/2018(ኢዜአ)፦ የአፍሪካ ህብረት እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ የፀጥታው ምክር ቤት ውክልናን ጨምሮ የባለብዙ ወገን አጀንዳዎች ላይ ያላቸውን ትብብር አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታወቁ።
39ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ የካቲት 7 እና 8 ቀን 2018 ዓ.ም በህብረቱ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ ይካሄዳል።
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ ከጉባኤው አስቀድሞ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ጋር ተወያይተዋል።
ውይይቱ በቀጣናዊ ሰላም እና ደህንነት፣ ዘላቂ ልማትና ሁሉን አቀፍ ኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን ላይ ያተኮረ ነው።
በተለይም የአፍሪካ የኢንዱስትሪ ዘርፍ፣ እሴት መጨመርና መዋቅራዊ ትራንስፎርሜሽን ለእድገት፣ ለስራ ፈጠራ እና ለዘላቂ መረጋጋት ቁልፍ ሚና እንደሚጫወቱ ተነስቷል።
የኮሚሽኑ ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ የህብረቱ እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አጋርነት ኢ-ተገማች በሆነው የዓለም ሁኔታ ውስጥ ሰላም፣ ደህንነትና ዘላቂ አጋርነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ነው ብለዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የአፍሪካ ህብረት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የባለብዙ ወገን ስትራቴጂካዊ አጋር መሆኑን ገልጸው አፍሪካ በዓለም ሰላም፣ ደህንነትና የባለብዙ ወገን ስርዓት ሪፎርም ወሳኝ ሚና እንዳላት ተናግረዋል።
በውይይቱ የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት አስቸኳይ ሪፎርም እንደሚያስፈልገውና አፍሪካ በምክር ቤቱ ቋሚ ውክልና ማግኘት እንደሚገባት ተነስቷል።
ባለስልጣናቱ ህብረቱ እና ተመድ የዓለም የፋይናንስ ስርዓት እንዲሻሻልና አፍሪካ ፍትሃዊ የፋይናንስ አቅርቦት እንድታገኝ የጀመሩትን የጋራ ስራ አጠናክረው ለመቀጠል መስማማታቸውን ኢዜአ ከህብረቱ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።