ጨፌው በክልሉ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ የልማት ስራዎች የተገኙ ስኬቶችና ውስንነቶች ላይ በስፋት ይወያያል - ኢዜአ አማርኛ
ጨፌው በክልሉ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ የልማት ስራዎች የተገኙ ስኬቶችና ውስንነቶች ላይ በስፋት ይወያያል
አዳማ፤ የካቲት 6/2018(ኢዜአ)፦ የጨፌ ኦሮሚያ በክልሉ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ የልማት ስራዎች የተገኙ ስኬቶችና ውስንነቶች ላይ በስፋት እንደሚወያይ አፈ-ጉባኤ ሰዓዳ አብዱራህማን ገለፁ።
የጨፌ ኦሮሚያ 6ኛ የስራ ዘመን 5ኛ ዓመት 10ኛ መደበኛ ጉባኤ ነገ በአዳማ ገልመ ጨፌ መካሄድ ይጀምራል።
የጨፌ ኦሮሚያ አፈ-ጉባኤ ሰዓዳ አብዱራህማን ጉባኤውን በማስመልከት መግለጫ በሰጡበት ወቅት ጨፌው በክልሉ ያለፉት ስድስት ወራት የመንግስት የስራ አፈጻጸም ዕቅድ ክንውን ላይ ውይይት ያደርጋል ብለዋል።
በተለይ በግማሽ ዓመቱ የክልሉ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ የልማት ስራዎች የተገኙ ስኬቶችና ውስንነቶች ላይ ይወያያል ነው ያሉት።
በተጨማሪም የጨፌው አባላትና ቋሚ ኮሚቴዎች በወረዳዎች፣ በከተሞችና በዞኖች ባደረጉት የክትትልና ቁጥጥር እንዲሁም በመስክ ምልከታ የተገኙ ሪፖርቶች ለጉባኤው ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸውም ጠቁመዋል።
ጉባኤው የዳኞች ሹመትን ጨምሮ የተለያዩ አጀንዳዎች ላይ በጥልቀት በመወያየት ያፀድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅም አመልክተዋል።