ለግብርና ልማት ሥራ ውጤታማነት በተሰጠው ትኩረት ተጠቃሚነታችን እያደገ ነው -አርሶ አደሮች - ኢዜአ አማርኛ
ለግብርና ልማት ሥራ ውጤታማነት በተሰጠው ትኩረት ተጠቃሚነታችን እያደገ ነው -አርሶ አደሮች
ሚዛን አማን ፤ የካቲት 6/2018(ኢዜአ)፦መንግሥት ለግብርና ልማት ሥራ ውጤታማነት በሰጠው ትኩረት ተጠቃሚነታቸውን እያሳደጉ መሆኑን በሸካ ዞን የየኪ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለጹ።
የወረዳው አርሶ አደሮች ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማትና የሌማት ትሩፋት መርሀግብሮችን ጨምሮ ሌሎች የግብርና ኢኒሼቲቮች የኢኮኖሚ አማራጮችን በማስፋት ገቢያቸውን እያሳደጉ ነው።
ከአስተያየት ሰጪዎች መካከል አርሶ አደር ጣሃ ሐቢብ እንዳሉት በቆሎ፣ ማሽላ፣ ቡና፣ ቁንዶ በርበሬ፣ እርድና ዝንጅብል በማልማት ኑሯቸውን እየመሩ ነው።
ከግብርና ልማት ሥራቸውም ከዚህ ቀደም ከሚያገኙት የተሻለ ምርት በማምረት ገቢያቸውን እያሳደጉ መምጣታቸውን ተናግረዋል።
ምርቶችን በጥራት አምርተን የልፋታችንን ያህል ውጤት እንድናገኝ በመንግስት በኩል የተሻሻለ ዝርያና የግብርና ግብአት አቅርቦት ድጋፍ ይደረግልናል ያሉት አርሶ አደር ጣሃ፣ የመንግስት እገዛና ክትትል ለስኬታማነታቸው አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
የሌማት ትሩፋት መርሀግብር፣ የገጠር ኮሪደር እና መሰል የመንግሥት የልማት ኢኒሼቲቮች የኢኮኖሚ ምንጭ በመሆን የአርሶ አደሩን ሕይወት እያሻሻሉ መሆኑንም አክለዋል።
የበጋ መስኖ ስንዴ፣ የሩዝና መሰል የሰብል ልማት ሥራዎች ተጠናክረው ከቀጠሉ የቤተሰብ የምግብ ዋስትናን የሚያረጋግጡ ናቸው ያሉት ደግሞ አርሶ አደር አያሌው ኃይሉ ናቸው።
በተለይ በቡና እና በቅመማ ቅመም ምርት የተሻለ ገቢ በማግኘት ለውጥ እንዲያመጡ ምቹ ሁኔታ እንደተፈጠረላቸው ነው የገለጹት።
የተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎችን በምርምር ተቋማት በኩል መንግሥት እያቀረበ በመሆኑ በማሳቸው አላምደው ምርታማነታቸውን እያሳደጉ መሆኑን የገለጹት ደግሞ አርሶ አደር ታምራት እረና ናቸው።
ሩዝን ጨምሮ በአካባቢው ያልተለመዱ ሰብሎችን በማልማት ውጤታማ መሆን እንደተቻለ ጠቅሰው መንግሥት ለግብርና ልማት የሰጠው ትኩረት ምርታማነታችንን የሚያሳድጉ ናቸው ብለዋል።
የእርሻ ሥራቸው ውጤታማ እየሆነ በመምጣቱ ምርታቸውን ከቤት ፍጆታ ባለፈ ለገበያ በማቅረብ ገቢያቸውን እያሳደጉና ጥሪት እያፈሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የሸካ ዞን ግብርና፣ ደን፣ አካባቢ ጥበቃና ኅብረት ሥራ መምሪያ ኃላፊ አቶ አዕምሮ ደሳለኝ፤ በዞኑ የግብርና ኢኒሼቲቭ ሥራዎች በአርሶ አደሮች ማሳ እንዲተገበሩ የተሰራው ሥራ ውጤት እያመጣ መሆኑን ተናግረዋል።
ለአብነትም በ10 አርሶ አደሮች ማሳ ከአራት ዓመት በፊት የተጀመረው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ዘንድሮ ከ2ሺህ 500 በሚበልጡ አርሶ አደሮች ማሳ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።
በተመሳሳይ በ300 ሄክታር ማሳ ላይ የተጀመረው የሩዝ ልማት ዘንድሮ ወደ 3ሺህ 200 ሄክታር ማደጉን ገልጸው፣ በሌማት ትሩፋትም እየመጣ ያለው ውጤት እንዲጠናከር በመምሪያው በኩል ድጋፍና ክትትሉ መጠናከሩን ጠቁመዋል።