በጤና ዘርፍ የሚደረግ ኢንቨስትመንት ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማረጋገጥ ትልቅ መሠረት ይጥላል - ኢዜአ አማርኛ
በጤና ዘርፍ የሚደረግ ኢንቨስትመንት ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማረጋገጥ ትልቅ መሠረት ይጥላል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 6/2018(ኢዜአ)፦ በጤና ዘርፍ ላይ የሚደርግ ኢንቨስትመንት የሀገርን ምርታማነት ከማሳደግ ባለፈ ለዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት ትልቅ መሠረት መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ድጉማ ገለጹ።
ሚኒስትር ዴኤታው ይህንን የገለጹት “በኢትዮጵያ የወደፊት ዕድል ላይ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ፤ ከጤና ወጪ ወደ ጤና ኢንቨስትመንት” በሚል መሪ ሀሳብ በተዘጋጀው የዘላቂ ጤና ፋይናንስ የንቅናቄ ወርክሾፕ ላይ ነው።
ዶክተር ደረጀ ድጉማ በዚሁ ወቅት፤ መንግሥት ለጤናው ዘርፍ የሚመድበው በጀት ጤናማና አምራች ዜጋን በመፍጠር በኩል የላቀ ድርሻ አለው ብለዋል።
እስካሁን ባለው ሂደትም በርካታ የጤና ተቋማት ተገንብተው ለአገልግሎት መብቃታቸውና ዘመናዊና ወሳኝ የሕክምና መሣሪያዎችን የማሟላት ሥራ፣ ብቁና በቂ የሰው ኃይል የማፍራት ተግባር መከናወኑን ተናግረዋል፡፡
መንግሥት በቀጣይ የዘርፉን ውጤታማነት ለማሳደግ ዘላቂ የፋይናንስ ሥርዓት መዘርጋትን እንደ ቀዳሚ ተግባር መያዙንም ጠቅሰዋል፡፡
የጤና ፋይናንስ ሥርዓቱ አስተማማኝ ወደ ሆኑ የሀገር በቀል የፋይናንስ ምንጮች መሸጋገር እንዳለበትም ነው የገለጹት፡፡
ይህንን ግብ ለማሳካትም በርካታ ተግባራት እንደሚከናወኑ ጠቁመው የፋይናንስ ምንጮችን በሀገር ውስጥ አቅም ማጠናከር፣ የጤና መድህን ሽፋንን በስፋት ማዳረስ እንዲሁም የግል ባለሀብቶችና አጋር አካላት በዘርፉ እንዲሳተፉ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ጤናማ ዜጋ ለሀገር እድገት ያለው ሚና የማይተካ መሆኑን በመጥቀስ፡፡
በመድረኩ የተገኙት በኢትዮጵያ የዓለም ጤና ድርጅት(WHO) የስትራቴጂክ ጤና ፖሊሲና ፕላን አስተባባሪ ዶክተር ቢጆይ ፒ. ናምቢያር፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ዘርፉን ለማዘመን እየከወናቸው ያሉ ተግባራት የሚደነቁ ናቸው ብለዋል።
ኢትዮጵያ የራሷን ዘላቂ የጤና ፋይናንስ ለማረጋገጥ የጀመረችው እንቅስቃሴ ወቅታዊና ስትራቴጂካዊ መሆኑንም ጨምረው ጠቁመዋል፡፡