ቀጥታ፡

የአገልግሎት አሰጣጥ መዘመንና የመሰረተ ልማት መሟላት ኢትዮጵያን ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ እያደረጋት ነው 

ኮምቦልቻ  ፤ የካቲት 6/2018(ኢዜአ)፦የአገልግሎት አሰጣጥ መዘመንና የመሰረተ ልማት መሟላት ኢትዮጵያን ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ እያደረጋት መሆኑን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን(ዶ/ር) ገለጹ።

በኮሚሽኑ የፌዴራል፣ የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የኢንቨስትመንት አስፈጻሚዎች የጋራ የምክክር መድረክ በኮምቦልቻ እየተካሄደ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን(ዶ/ር)፤የተለያዩ መሰረተ ልማቶችን በማሟላትና አገልግሎት አሰጣጡን በማዘመን የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን መሳብ ተችሏል ብለዋል።


 

በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት በዘርፉ ላይ ከፍተኛ መነቃቃት መፈጠሩን ጠቅሰው፤ ከ2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር በላይ ካፒታል ያላቸው የውጭ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን ማፍሰሳቸውን ተናግረዋል።

ይህም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ20 በመቶ ጭማሬ አለው ብለዋል።

አክለውም በፌዴራል ደረጃ ለ245 የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፍቃድ መሰጠቱን ገልጸዋል።

ባለፉት ስድስት ወራት የቻይና፣ የህንድ፣ የአሜሪካ፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስና የሌሎች አገራት ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ ኢንቨስትመንት ዘርፎች ለመሰማራት ፍቃድ መውሰዳቸውን ተናግረዋል።

የአገልግሎት አሰጣጡ መዘመንና የመሰረተ ልማት መሟላት ኢትዮጵያን ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ እያደረጋት መሆኑንም ኮሚሽነሩ አመልክተዋል። 


 

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል የከተማ ልማት ክላስተር አስተባባሪ አህመዲን መሀመድ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የክልሉን ሰላም በማጽናት የኢንቨስትመንት ዘርፉን ለማሳደግ የተጀመሩ ሥራዎች አበረታች ውጤት እያስመዘገቡ ናቸው ብለዋል።

ባለፉት ስድስት ወራት በክልሉ ከፍተኛ ሃብት ላስመዘገቡ የውጭና የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱን ጠቁመው፣ የመሰረት ልማቱንና አገልግሎት አሰጣጡን በማሻሻል ወደ ሥራ እንዲገቡም እየተደረገ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም