የቤተሰብን የኢኮኖሚ አቅም በማሳደግ የመቀንጨር ችግርን ለማስወገድ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የቤተሰብን የኢኮኖሚ አቅም በማሳደግ የመቀንጨር ችግርን ለማስወገድ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ነው
ሰቆጣ ፤ የካቲት 6/2018(ኢዜአ)፦የቤተሰብን የኢኮኖሚ አቅም በማሳደግና የአመጋገብ ሥርዓትን በማሻሻል የመቀንጨር ችግርን ለማስወገድ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ።
የሰቆጣ ቃልኪዳን ስምምነት (Sekota Declaration) መንግስት በ2030 ዓ.ም በሀገሪቱ የሚስተዋለውን የህፃናት የተመጣጠነ ምግብ እጥረትና የመቀንጨር ችግር ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት የገባው ቁርጠኝነት ነው።
ነፍሰ-ጡር እናቶችና ከ5 ዓመት በታች ህፃናት ስርዓተ-ምግብን ማሻሻል፣ ምርታማነትን ማሳደግና አዕምሯዊና አካላዊ ዕድገት ቀውሶችን መከላከል የስምምነቱ ዋነኛ ግብ ነው።
የመቀንጨርና የመቀጨጭ ችግር ከሚስተዋልባቸው አካባቢዎች አንዱ ዋግ ኽምራ ነው።
የብሔረሰብ አስተዳደሩ ይህን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ሥርዓተ ምግብን የሚያሻሽሉ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።
የሰቆጣ ቃል-ኪዳን ስምምነት እውን ከሚሆንባቸው ተግባራት አንዱ ሴቶችና እናቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡበት ሁኔታን መፍጠር ነው።
ይህን ለማድረግ ከተወሰዱ እርምጃዎች አንዱ እናቶችን በእንስሳት ልማት ዘርፍ በማሰማራት የራሳቸውን ገቢ ከማመንጨት ባለፈ ለቤተሰቦቻቸው የተመጣጠነ ምግብ ማቅረብ የሚችሉበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነው።
በብሔረሰብ አስተዳደሩ በእንሰሳት እርባታ ዘርፍ የሥራ ዕድሉ ከተፈጠረላቸው እናቶች መካከል ሙሉ እሚያምረው አንዷ ናቸው።
እርሳቸው እንደሚሉት፣ በተደረገላቸው የእንቁላል ጣይ ዶሮዎች ድጋፍ ከዕለት ፍጆታ ባለፈ ለገበያ እያቀረቡ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል።
ለራሳቸውና ለልጆቻቸው እንቁላልን ጨምሮ የተለያዩ የምግብ አይነቶችን በመመገብ ሥርዓተ-ምግባቸውን ለማሻሻልና ጤናቸውን በአግባቡ ለመጠበቅ እንዳስቻላቸውም ተናግረዋል።
የጋዝጊብላ ወረዳ ነዋሪዋ አታላ ውቤ፤ ከዶሮ እርባታ ባለፈ በጓሮ አትክልትና ፍራፍሬ በመሰማራት የቤተሰቦቻቸውን አመጋገብ ሥርዓት ማሻሻል እንደቻሉ ይገልጻሉ።
በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የእንስሳትና ዓሳ ሃብት ልማት መምሪያ ኃላፊ ሲሳይ አያሌው እንደገለጹት፣ በእንስሳት እርባታ ዘርፍ የስርዓተ-ምግብን የሚያሻሽሉ ስራዎች እየተሰሩ ነው።
የሰቆጣ ቃል ኪዳን ፕሮጀክትና ግብረ ሰናይ ድርጅቶች የሕብረተሰቡ የአመጋገብ ሥርዓት እንዲሻሻል አጋዥ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን ገልጸዋል።
በ2018 በጀት ዓመት 20 ሺህ 800 የሚያጠቡና ነፍሰ ጡር እናቶችን በእንስሳት እርባታ ዘርፍ ለማሰማራት ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን አስታውሰው፣ ባለፉት ስድስት ወራት ከ12 ሺህ በላይ እናቶችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
እናቶች በዶሮ፣ በፍየልና በላም እርባታ ላይ እንዲሰማሩ በማድረግ የልጆቻቸውንና የራሳቸውን የአመጋገብ ሥርዓት እንዲያሻሽሉና ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኙ ዕድል መፈጠሩን ነው ያብራሩት፡፡