ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ለአፍሪካውያን አንድነትና ትብብር የምታበረክተው አስተዋጽኦ የአህጉሪቱን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ውህደት ለማፋጠን ያላትን ቁርጠኝነት ያሳያል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 6/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ለአፍሪካውያን አንድነትና ትብብር የምታበረክተው አስተዋጽኦ የአህጉሪቱን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስርና ውህደት ለማፋጠን ያላትን ቁርጠኝነት ያሳያል ሲሉ የኢኳቶሪያል ጊኒ የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ማሪ-ክሩዝ ኢቩና አንዴሜ ገለጹ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአፍሪካውያን የችግር ጊዜ ደራሽ፣ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ማስተሳሰሪያ ድልድይ መሆኑንም ገልጸዋል።

የአፍሪካ ሕብረት 48ኛው የሥራ አስፈፃሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ትናንትና ከትናንት በስቲያ ለሁለት ተከታታይ ቀናት በአዲስ አበባ የሕብረቱ ዋና መስሪያ ቤት ሲካሄድ ቆይቶ ትናንት ተጠናቋል።

39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔም "ዘላቂ የውሃ አቅርቦትና ደህንነቱ የተጠበቀ የንጽህና አጠባበቅ ስርዓቶችን ማረጋገጥ፤ ለአጀንዳ 2063 ግቦች ስኬታማነት” በሚል መሪ ሀሳብ ነገና ከነገ በስትያ ይካሄዳል።

የጉባኤው ተሳታፊ የኢኳቶሪያል ጊኒ የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ማሪ-ክሩዝ ኢቩና አንዴሜ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ለደቡብ ደቡብ ትብብር መጎልበት ቁርጠኛ አቋም ያላት ሀገር ናት።

ኢትዮጵያ በአህጉራዊ አንድነት ላይ ያላት ቁርጠኛ አቋም የደቡብ-ደቡብ ትብብርን በማጠናከር ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ውህደትን ለማፋጠን ከፍተኛ አቅም እየሆነች እንደምትገኝም ገልጸዋል።

ለአብነትም ከዓመታት በፊት የተከሰተው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሥርጭትን ለመከላከል በተደረገው አህጉራዊ ጥረት ኢትዮጵያ የሕክምና ቁሳቁሶችን ለአፍሪካ ሀገራት በማዳረስ አስደናቂ አጋርነቷን በተግባር አሳይታለች ብለዋል።


 

የኢትዮጵያ አየር መንገድም የወረርሽኝ መከላከያ መድኃኒትና ቁሳቁሶችን ለአፍሪካውያን በማዳረስ የችግር ጊዜ ደራሽ መሆኑን በተግባር ያስመሰከር ተቋም መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የገነባው የተደራሽነት አድማስም የአፍሪካ ሀገራትን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር በማጠናከር አይነተኛ ሚና እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህም ኢትዮጵያ መሠረተ ልማቷን ለአፍሪካ እያጋራች መሆኑን ያሳያል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ በምስራቅ አፍሪካ የኢኮኖሚ ውህደትም የመሪነት ሚና እየተወጣች ትገኛለች ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ መሆኗ በአህጉራዊ ጉዳዮች ላይ ግንባር ቀደም ተዋናይነቷን በማጉላት የአፍሪካውያን አስተሳሳሪ ዋልታ እንድትሆን ማስቻሉን ገልጸዋል።

የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤን በየዓመቱ በስኬት በማስተናገድ አህጉራዊ ትብብሮችን ለማጎልበት ትልቅ አቅም እየሆነች እንደምትገኝም ነው ጨምረው የገለጹት።

ኢትዮጵያ ለአፍሪካውያን አንድነትና ትብብር የምታበረክተው አስተዋጽኦ የአህጉሪቱን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስርና ውህደት ለማፋጠን ያላትን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይም አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም