ምርጫው ፍጹም ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን የምክር ቤት አባላት ሚና ወሳኝ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ምርጫው ፍጹም ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን የምክር ቤት አባላት ሚና ወሳኝ ነው
አርባ ምንጭ ፤ የካቲት 6/2018(ኢዜአ)፦ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ፍጹም ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን የምክር ቤት አባላት ሚና ወሳኝ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አፈ- ጉባኤ አለማየሁ ባውዲ አመለከቱ።
የክልሉ ምክር ቤት 6ኛ ዙር 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 6ኛ መደበኛ ጉባኤውን በአርባ ምንጭ ከተማ ማካሄድ ጀምሯል።
ዋና አፈ ጉባኤ አለማየሁ ባውዲ በመክፈቻው መርሃ ግብር ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ጠቅላላ ምርጫው ፍጹም ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን የምክር ቤት አባላት ሚና ሰፊ ነው ብለዋል።
የለውጡ መንግስት የሀገራችንን ኋላ ቀር የፖለቲካ ልምምድ በመቀየር ሰው ተኮር የፖለቲካ ምህዳር በመትከል ሁለንተናዊ ልማት እያረጋገጠ ይገኛል ነው ያሉት።
የጋራ ሀገርና የጋራ ሃሳብ ላይ የተመሠረተ ገዢ ትርክት በመገንባት የህዝቡን አንድነትና አብሮነት ለማረጋገጥ በተከናወኑ ተግባራት ተጨባጭ ለውጥ እየተመዘገበ ይገኛል ብለዋል።
ምክር ቤቶች የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ተምሳሌት እንደመሆናቸው መጠን የህዝቡ የልማት፣ የዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲፈቱና የልማት ተጠቃሚነት ይበልጥ እንዲረጋገጥ የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባ አመልክተዋል።
በክልሉ ባለፉት ስድስት ወራት በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በፖለቲካዊ ዘርፎች የህዝቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ በርካታ ስኬቶች መመዝገባቸውን ዋና አፈ ጉባኤው በንግግራቸው አንስተዋል።
በክልሉ ያለውን ዕምቅ የግብርና አቅም ለመጠቀም የኩታ ገጠም እና የሜካናይዜሽን ልማትን ለማስፋፋት እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች ከልማዳዊ አሠራር በመውጣት ገበያን የሚያረጋጋ ምርት እንዲገኝ እያደረገ ስለመሆኑ ተናግረዋል።
በመሠረተ ልማት፣ በትምህርትና በሌሎችም ዘርፎች ፍትሃዊ ተደራሽነትን በማረጋገጥ ህዝብን ተጠቃሚ ያደረጉ ሰፊ ስራዎች መሰራታቸውን ገልጸዋል።
አቶ አለማየሁ፤ በክልሉ የተከሰተውን የማርበርግ ቫይረስ በህዝብና በአመራሩ የተቀናጀ ተግባር መቆጣጠር መቻሉንም አመልክተዋል።
ክልሉን የሰላም፣ የመቻቻልና የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ በተደረጉ ጥረቶች በሁሉም አካባቢ ለውጥ ተመዝግቧል ብለዋል።
ለሁለት ቀናት በሚቆየው መደበኛ ጉባኤም የክልሉ መንግስት የ2018 ዓ.ም ግማሽ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ማድመጥና ማጽደቅን ጨምሮ ልዩ ልዩ አዋጆችና ደንቦች እንዲሁም ሹመቶች እንደሚፀድቁም ይጠበቃል።