ቀጥታ፡

በአፍሪካ የጤና ዋስትናን ለማረጋገጥ ቀጣናዊ ትስስርንና ሁሉን አቀፍ ትብብርን ማጠናከር ወሳኝ ነው

አዲስ አበባ፤ የካቲት 6/2018(ኢዜአ)፦ በአፍሪካ የጤና ዋስትና እና ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ቀጣናዊ ትስስርንና ሁሉን አቀፍ ትብብርን ማጠናከር ወሳኝነት እንዳለው የኢፌዴሪ ጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለፁ።

የአፍሪካ የበሽታ መከላከል እና መቆጣጠር ማዕከል ከአፍሪካ ልማት ባንክና ከአፍሪካ ህብረት የልማት ኤጀንሲ 'አውዳ-ኔፓድ' ጋር በመተባበር የአፍሪካ የጤና ዋስትና እና ሉዓላዊነት አጀንዳን ማሳካት በሚያስችሉ የፋይናንስ አማራጮች ላይ ያተኮረ ውይይት እየተካሄደ ነው።

የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በአፍሪካ የጤና ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ የሚያስችሉ የክትትልና ስትራቴጂክ ፖሊሲዎች ላይ የተሻሉ ስራዎች ተሰርተዋል።

አፍሪካ የጤና ዋስትና እና ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ እንደምትገኝ አንስተው፤ የአፍሪካ ሲዲሲ የአህጉሪቱ የህብረተሰብ ጤና ላይ ፖለቲካዊ፣ ስልታዊ እና ቴክኒካዊ አመራር እንዲሰጥ በአፍሪካ ህብረት የተሰጠው ውሳኔ ይህን የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።

ተለዋዋጭ በሆነ ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ፣ ተደጋጋሚ ወረርሽኞች እየገጠሙ ባሉበት እና የውጭ ድጋፎች ባልተጠበቀ ሁኔታ እየቀነሱ መምጣት በአህጉሪቱ የዘርፉ ስራ ላይ ተጽዕኖ ከማሳደሩ በላይ በውጭ ድጋፍ ላይ ያለንን ጥገኝነት ያሳየ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በመሆኑም አህጉራዊ አቅምን በማጠናከር ቀጣናዊ ትብብርን ማስፋት፣ የሀገር ውስጥ የቴክኒክ አቅምን ማጎልበት፣ ጠንካራ አስተዳደር መዘርጋት ለወደፊት አደጋዎች ዝግጁ ለመሆን ወሳኝ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የአጭር ጊዜ የአደጋ ጊዜ የገንዘብ ምንጭን ወደ አስተማማኝ የረጅም ጊዜ ኢንቨስትመንት መቀየር እንዲሁም በሀገር ውስጥ ማምረት የሚያስችል የመሠረተ ልማት አቅምን መገንባት እንደሚገባም ጠቁመዋል።

ለዚህም የአፍሪካ ልማት ባንክ የመድኃኒትና የክትባት ምርትን ለመደገፍ የላቀ ሚና እንደሚኖረው ነው ሚኒስትሯ የገለጹት።

የአፍሪካ ልማት ባንክ በፋይናንስ፣ የቀጣናዊ አጋሮች ቅንጅት፣ የግል ባለሀብቶች ተሳትፎ እንዲሁም የመንግሥታት ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት አስፈላጊ መሆኑንም አንስተዋል።

ትልምን ወደ ተግባር መቀየር፣ ተቋማትን ማጠናከር፣ ቀጣናዊ አቅምን መገንባትና የሀገር ውስጥ ምርትን ማሳደግ ግድ የሚልበት ወቅት መሆኑን አንስተው፤ የፋይናንስ ውጤታማነትንና የአፍሪካን የጤና ሉዓላዊነት ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።

የውይይት መድረኩ የአፍሪካን ጤና ዋስትና ለማረጋገጥና ዘላቂ የጤና ፋይናንስ ዘመን ለማራመድ ያለን የጋራ ቁርጠኝነት ነጸብራቅ ነው ሲሉም ገልጸዋል።

በውይይቱ የአፍሪካ የበሽታ መከላከል እና መቆጣጠር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጄን ካሳይ፣ የአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት ሲዲ ኦልታ(ዶ/ር)፣ የአፍሪካ ህብረት የልማት ኤጀንሲ ዋና ስራ አስፈፃሚ ናርዶስ በቀለ፣ የአፍሪካ ሀገራት የጤናና ፋይናንስ ሚኒስትሮችና ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም