7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሀገር የምታሸንፍበት እንዲሆን በቅንጅት እንሰራለን-የተፎካካሪ ፓርቲዎች - ኢዜአ አማርኛ
7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሀገር የምታሸንፍበት እንዲሆን በቅንጅት እንሰራለን-የተፎካካሪ ፓርቲዎች
ባህርዳር፤ የካቲት 6/2018(ኢዜአ)፦ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሀገር የምታሸንፍበት እንዲሆን ቅንጅታቸውን የበለጠ እንደሚያጠናክሩ በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ገለጹ።
''ለሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ በጋራ እንቁም'' በሚል መሪ ሃሳብ በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ የተፎካካሪ ፖርቲዎች የጋራ ምክር ቤት መድረክ በባህር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።
የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ ተስፋሁን አለምነህ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊና አሳታፊ እንዲሆን የፖለቲካ ፓርቲዎች ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው።
ምርጫው ሕግና አሰራርን ተከትሎ ሁሉም ፓርቲዎች በነፃነት የሚሳተፋበትና በሕዝብ ዘንድ አመኔታ ያተረፈ እንዲሆን ትብብርን የበለጠ ማጠናከር ይገባል ብለዋል።
የጋራ ምክር ቤቱ ስልጡን ፖለቲካን በማራመድ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት እየሰራ መሆኑን አንስተዋል።
በምርጫ አሸናፊና ተሸናፊ መኖሩ ተፈጥሯዊ ቢሆንም በፋክክር ሂደቱ እኩል በመሳተፍ በምርጫው ሀገር እንድታሸንፍ ለማድረግ ቅንጅታዊ አሰራሩን ማጠናከር ይገባል ብለዋል።
ምክር ቤቱ ምርጫው ሰላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊ፣ ፍትሃዊና አሳታፊ እንዲሆን ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ኃላፊነቱን እንደሚወጣ አረጋግጠዋል።
በምርጫ ሂደቱ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በሰለጠነ መንገድ መፍታት ተገቢ መሆኑን አስገንዝበዋል።