የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ የተለያዩ አዋጆችና ሹመቶችን በማፅደቅ ተጠናቀቀ - ኢዜአ አማርኛ
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ የተለያዩ አዋጆችና ሹመቶችን በማፅደቅ ተጠናቀቀ
ታርጫ ፤ የካቲት 6/2018(ኢዜአ)፦ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ የተለያዩ አዋጆችን፣ ተጨማሪ በጀትና ሹመቶችን በማፅደቅ ተጠናቀቀ።
የክልሉ ምክር ቤት 6ኛ ዙር 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 9ኛ መደበኛ ጉባኤ በሁለተኛ ቀን ውሎው የተለያዩ አዋጆችን፣ ተጨማሪ በጀትና ሹመቶችን በማፅደቅ ተጠናቋል።
በጉባኤውም ወደ ከተማ የተካለሉ ቀበሌዎችን የተመለከተ ሞሽን የቀረበ ሲሆን ይህም በየመዋቅሩ የሚከናወኑ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ለህዝቡ ተደራሽ እንዲሆኑ ለማድረግ ያለመ መሆኑ ተጠቁሟል።
በዚህም መሰረት ከሸካና ቤንች ሸኮ ዞኖች 10 ቀበሌዎች ሙሉ በሙሉና በከፊል ወደ ቴፒና ሸኮ ዞኖች እንዲካለሉ በቀረበው የድጋፍ ሞሽን ላይ የምክር ቤቱ አባላት ውይይት አካሄደዋል።
ሞሽኑን በተመለከተ ጥያቄና አስተያየቶች ቀርበው ምላሽ ከተሰጠበት በኋላ በአዋጅ ቁጥር 3/2018 ሞሽኑ በሙሉ ድምፅ ፀድቋል።
እንዲሁም ለኢኮኖሚው እገዛ ለማድረግ የሚያስችል የገቢ ግብር ማሻሻያ ረቂቅ ደንብ ቀርቦ ውይይት ከተደረገ በኋላ በአዋጅ ቁጥር 49/2018 በሚል በሙሉ ድምፅ ሊፀድቅ ችሏል።
በክልሉ ምክር ቤት ተጨማሪ የበጀት ረቂቅ ላይ ውይይት በማድረግ ለካፒታል ፕሮጀክቶች ማስፈፀሚያ የሚውል 657 ሚሊዮን 600 ሺህ ብር ተጨማሪ በጀትን ምክር ቤቱ በሙሉ ድምፅ አፅድቆታል።ምክር ቤቱ በሁለተኛ ቀን ውሎውም ሌሎች አዋጆችን ማፅደቁም ተመልክቷል።
በተጨማሪም ምክር ቤቱ ለተለያዩ የሥራ ክፍሎች የቀረቡ እጩዎችን በሙሉ ድምፅ አፅድቋል። በዚህም መሰረት፤-
1. አቶ ንጉሴ ወልደጊዮርጊስ፤ የክልሉ ሰው ሀብትና ፐብሊክ ሰርቪስ ቢሮ ኃላፊ
2. ረዳት ፕሮፌሰር ዘመድኩን ሰለሞን ፤የኢንዱስትሪና ኢኖቬሽን ቢሮ ኃላፊ
3. አቶ መቱ አኮ፤ የክልሉ ቆላማና እና አርብቶ አደር አካባቢዎች ቢሮ ኃላፊ
5. አቶ ታሪኩ አካሉ፤ የክልሉ ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ እንዲሁም ሌሎች ሽግሽግ የተደረገባቸው ኃላፊዎች ዝርዝር ቀርቦ በምክር ቤቱ በሙሉ ድምፅ ፀድቋል።
ተሿሚዎችም በምክር ቤቱ ፊት ቀርበው ቃለ መሃላ ፈጽመዋል ።