ቀጥታ፡

በጅማ ከተማ እየተገነባ ለሚገኘው የስማርት ሲቲ ፕሮጀክት የ12 ኪሎ ሜትር የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ ተከናወነ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 6/2018(ኢዜአ)፦ በጅማ ከተማ እየተገነባ ለሚገኘው የስማርት ሲቲ ፕሮጀክት 12 ኪሎ ሜትር የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ መከናወኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።

አገልግሎቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳመላከተው በጅማ ከተማ እየተገነባ ለሚገኘው የስማርት ሲቲ ፕሮጀክት መጠነ ሰፊ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ዝርጋታ እየተከናወነ ይገኛል፡፡

ለፕሮጀክቱ ከጅማ አዲሱ ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ 12 ኪሎ ሜትር የሚረዝም 15 ኪሎ ቮልት ወጪ መስመር ዝርጋታ እና 300 የመካከለኛ መስመር ምሰሶ ተከላ ተከናውኗል ብሏል፡፡



 

በተመሳሳይ ሁለት ባለ 1ሺህ 250 ኪሎ ቮልት አምፒር፣ አንድ ባለ 630 ኪሎ ቮልት አምፒር ኮምፓክት ትራንስፎርመርና አንድ ባለ 200 ኪሎ ቮልት አምፒር ትራንስፎርመሮች መተከሉንም አገልግሎቱ ገልጿል፡፡

ከኃይል ማከፋፈያ ጀምሮ እስከ ፕሮጀክቱ ያለው የመካከለኛ መስመር ዝርጋታ በሶስት ወራት በማጠናቀቅ ካለፈው ሐምሌ ወር ጀምሮ ለፕሮጀክቱ 5 ሜጋ ዋት ኃይል ማቅረብ ተችሏል ነው ያለው፡፡


 

የማሰራጫ መስመሩን ደረጃ የማስጠበቅና በኮንክሪት የመቀየር ስራውም 85 በመቶ መድረሱን አገልግሎቱ አስታውቋል፡፡

አሁን ላይ ለስማርት ከተማው የቀረበው የኃይል መጠን 5 ሜጋ ዋት ቢሆንም በቀጣይ ለሚከናወኑ ሌሎች ትልልቅ ግንባታዎች ተጨማሪ 20 ሜጋ ዋት ኃይል ለማቅረብ እየተሠራ ይገኛል ነው ያለው በመግለጫው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም