ቀጥታ፡

የሠመራ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መጉላላትን አስቀርቷል

ሠመራ፤ የካቲት 6/2018(ኢዜአ)፦ የሠመራ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ጉዳያቸውን በፍጥነት በመጨረስ መጉላላትን እንዳስቀረላቸው የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ተናገሩ።

የሰመራ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ፣ የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሸነር መኩሪያ ኀይሌ(ዶ/ር) እና የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ በተገኙበት ህዳር 8 ቀን 2018 ዓ.ም ተመርቆ ስራ መጀመሩ ይታወሳል።

ማእከሉ ለደንበኞች  የተቀላጠፈ አገልግሎት በመስጠት የተገልጋዩን እርካታ በማሳደጉ ተግባሩን ወደ ሌሎች  የክልሉ ከተሞች የማስፋት ስራ እንደሚሰራም ተገልጿል።

ማዕከሉ የዘረጋው የተቀላጠፈ  አገልግሎት ጊዜና ገንዘባቸውን ከብክነት በማዳን እንግልትን እንዳስቀረላቸው የሰመራ ሎጊያ ነዋሪዎች ለኢዜአ ገልጸዋል።

የአገልግሎት አሰጣጡን  አስመልክቶ ሀሳባቸውን ከሰጡ ተገልጋዮች  መካከል የሠመራ ከተማ ነዋሪው አቶ ሀቢብ መሐመድ፤ የሰመራ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የተለያዩ  መስሪያ ቤቶችን በአንድ ላይ በማግኘት በአጭር ጊዜ  ጉዳያቸውን ለመጨረስ እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።


 

ይህም ከመጉላላትና ከተጨማሪ ወጪዎች እንደታደጋቸውና ጊዜያቸውን በተገቢው እንዲጠቀሙ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል።

ማዕከሉ የተለያዩ ተቋማትን አገልግሎቶች አቀናጅቶ መያዙ ጠቀሜታው የጎላ ነው ያሉት ደግሞ የከተማዋ ነዋሪ ያሲን ሁሴን ናቸው።


 

ይህም በተለይም ከንግድ ፈቃድ ዕድሳት ጋር ተያይዞ ይወስድ የነበረውን ረጅም ጊዜ ማስቀረት የቻለ መሆኑን ተናግረዋል።

የሠመራ ሎጊያ ነዋሪው አቶ አህመድ መሐመድ በበኩላቸው፤ ማዕከሉ በአንድ ቦታ በመሆኑና በቴክኖሎጂ በመታገዝ አገልግሎት ማግኘት  ችያለሁ ብለዋል።


 

የሠመራ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ከሊል አሊ፤ ማዕከሉ በአምስት ተቋማትና በ13 አገልግሎት ዘርፎች አገልግሎት መጀመሩን አስታውሰው አሁን አገልግሎቱ ወደ 29 ዘርፎች ማደጉን ተናግረዋል።

በዚህም  በሶስት ወራት ውሰጥ 7ሺህ 800 ለሚሆኑ  ባለጉዳዮች  አገልግሎት መሰጠቱን ገልፀዋል።


 

ይህም የማህበረሰቡን እንግልትን እንዲሁም ብልሹ አሰራሮችን ለመቅረፍ በማገዙ ስራውን ይበልጥ በማስፋት የተገልጋዩን  እርካታ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም