የግብርና ሜካናይዜሽን አጠቃቀም ማደግ በሰብል ምርታማነት ላይ ተጨባጭ ውጤት አስገኝቷል - ኢዜአ አማርኛ
የግብርና ሜካናይዜሽን አጠቃቀም ማደግ በሰብል ምርታማነት ላይ ተጨባጭ ውጤት አስገኝቷል
ባህር ዳር ፤ የካቲት 6/2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል የግብርና ሜካናይዜሽን አጠቃቀም ማደግ በሰብል ምርታማነት ላይ ተጨባጭ ውጤት ማምጣቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለጸ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተጻፈው የመደመር መንግስት መጽሐፍ እንደተመላከተው፣ የእርሻ ሜካናይዜሽን ሽግግር የቅድሚያ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው።
በመሆኑም ዘመናዊ የእርሻ ማሽነሪዎችን ወደ እርሻ ማምጣትና አርሶ አደሩን ማስታጠቅ ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ በመሆኑ አርሶ አደሩ ትራክተሮችን በቁጠባና በብድር የሚያገኝበት መንገድ እየተተገበረ መሆኑን መጽሐፉ ያብራራል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አጀበ ስንሻው፤ መንግስት በዘንድሮው የበጀት ዓመት በግብርናው ዘርፍ ለማስመዝገብ የያዘው እቅድ እንዲሳካ ዘመናዊ የእርሻ መሳሪያዎችን መጠቀም ወሳኝ መሆኑን ያነሳሉ።
የግብርና ሜካናይዜሽን የሰብል ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግና ግብርናውን ትራንስፎርም ለማድረግ ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል።
በክልሉ በበጀት ዓመቱ አንድ ሺህ 400 የእርሻ ትራክተሮችንና የሰብል ማጨጃና መውቂያ ኮምባይነሮችን ለአርሶ አደሩ፣ ለህብረት ስራ ማህበራትና ለባለሃብቶች ተደራሽ ለማድረግ ታቅዶ እስካሁን 536 ያህሉ መሰራጨቱን ገልጸዋል።
እንዲሁም 878 አነስተኛ የሰብል ማጨጃ መውቂያና የበቆሎ መፈልፈያ ማሽኖችና 5 ሺህ 48 የውሃ መሳቢያ ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ማድረግ መቻሉን ገልፀዋል።
በክልሉ የሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂ እየተስፋፋ መምጣት የሰብል ምርታማነትን በማሳደግ በኩል ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን አብራርተዋል።
በክልሉ በ2017/18 የምርት ዘመን በትራክተር አንድ ሚሊዮን 35 ሺህ ሄክታር መሬት ማረስ የተቻለ ሲሆን በዋና ዋና ሰብሎች አማካኝ የሰብል ምርታማነትን በሄክታር ከ37 ነጥብ 5 ኩንታል ወደ 41 ነጥብ 4 ኩንታል ማሳደግ ተችሏል ብለዋል።
ለምርታማነቱ መጨመር በዋናነት የተጠቀሰው የግብርና ሜካናይዜሽን መስፋፋት መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በግለሰብ አርሶ አደሮች ዘንድ የውሃ ፓምፖች አጠቃቀም ማደጉና አርሶ አደሩ በክላስተር በመደራጀት ቴክኖሎጂን መጠቀሙ እንዲሁም ሌሎች የግብርና ዘርፉን ውጤታማ የሚያደርጉ ስራዎች ለውጤቱ መገኘት ድርሻ አላቸው ብለዋል።
አርሶ አደሩ በትራክተር መሬቱን የማረስ ልምድና ፍላጎቱ በየጊዜው እየጨመረ መምጣቱን ጠቅሰው፤ መሬትን በትራክተር ማረስ የአፈር ለምነት እንዲጨምርና ውሃን በውስጡ አስርጎ እንዲይዝ ያደርጋል ነው ያሉት።
በእንጅባራ ከተማ የሚገኘው የአድማስ ዩኒየን ስራ አስኪያጅ መሰረት ወርቄ፤ የአርሶ አደሩ የሜካናይዜሽን የእርሻ ልምምድና ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል።
በተያዘው ዓመት ዩኒየኑ 21 ትራክተሮች ግዥ በመፈፀም ለአባል አርሶ አደሮች በተመጣጣኝ ዋጋ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም አርሶ አደሩ የሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂን በአግባቡ ተጠቅሞ ትርፍ ምርት በማምረት ለገበያ እያቀረበና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱን እያሳደገ ነው ብለዋል።