ቀጥታ፡

በከተማዋ እየተከናወኑ የሚገኙ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ንግድና ኢንቨስትመንትን እያነቃቁ ነው

ሳውላ፤ የካቲት 6/2018(ኢዜአ)፦በሳውላ ከተማ እየተከናወኑ የሚገኙ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች የከተማዋን ንግድና ኢንቨስትመንት እያነቃቁ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ።

የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ንጉሴ መኮንን (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ከተማዋ የሴክተር መስሪያ ቤቶች ማዕከል በመሆኗ አካባቢዋን ምቹና ሳቢ የማድረግ ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል።

በተያዘው ዓመት የሁለት ባለ ኮከብ ሆቴሎች ግንባታን ጨምሮ ሌሎች የንግድ ተቋማት የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደው የልማት ስራ መጀመራቸውንም  አስታውቀዋል።

ይህም የከተማዋን የገቢ አቅም ለማሳደግ እያስቻለ ሲሆን በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት ብቻ ከመደበኛ ገቢ 152 ሚሊዮን ብር  መገኘቱን አመልክተዋል።

በዘንድሮው ዓመት የተገኘው ገቢ ከአምና ተመሳሳይ ወቅት ከተገኘው 56 ሚሊዮን ብር ጋር ሲነፃፀርም ከፍተኛ ልዩነት እንደሚያሳይም ነው የተናገሩት።

በከተማዋ በአሁኑ ወቅት ከ5 ኪሎ ሜትር በላይ የሚሆን የመንገድ ከፈታን ጨምሮ የሁለት ድልድይ ግንባታን በማከናወን ነዋሪው ለረዥም ጊዜያት ሲያነሳቸው ለነበሩ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ተችሏል ነው ያሉት ።

በአሁኑ ወቅት በከተማዋ የሁለተኛው ዙር የኮሪደር ልማት ስራ የተጀመረ ሲሆን በአንደኛው ዙር የተካሔደው የአንድ ኪሎሜትር  የኮሪደር ልማት ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት መደረጉንም ነው የጠቀሱት።

በከተማዋ የቀበሌ 04 ነዋሪ አቶ ስዩም ሱምሳ፤ በሚኖሩበት አካባቢ የመሻገሪያ ድልድይ ባለመኖሩ ረጅም የእግር ጉዞ በማድረግ ከፍተኛ እንግልት ይደርስባቸው እንደነበር ይናገራሉ።

በአሁኑ ወቅት በከተማዋ ከተካሄደው የመሰረተ ልማት ግንባታ ውስጥ የመሻገሪያ ድልድይ እንዲኖር በመደረጉ ችግሩ መፈታቱን እና እፎይታ ማግኘታቸውን ነው የሚናገሩት።

በአካባቢው የመንገድ ከፈታ እና የድልድይ ግንባታ መካሔዱ ወደ ተለያዩ ቦታዎች የምናደርገውን የረጅም ርቀትና አድካሚ ጉዞ አስቀርቶልናል ያሉት ደግሞ የአካባቢው ነዋሪ የሆኑት ቄስ ዘርይሁን ገብረኪዳን  ናቸው።

ወጣት ተክሌ ካሻ በበኩሉ በከተማዋ እየተከናወኑ ባሉ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ከሌሎች ወጣቶች ጋር በመደራጀት የስራ እድል ተጠቃሚ መሆኑን ነው የተናገረው። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም