ቀጥታ፡

ለዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ የሲቪክ ማህበራት ዝግጅት ምን ይመስላል?

ቦንጋ፤ የካቲት 6/2018(ኢዜአ)፦ ዘንድሮው በሚከናወነው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሂደት እንዲሁም ለዜጎች የነቃ ተሳትፎ የላቀ ሚናቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የሚገኙ የሲቪክ ማህበራት ድርጅቶች ገለጹ።

የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሂደት ተግባራዊ እንቅስቃሴ ተጀምሮ የፖለቲካ ፓርቲዎች እጩዎቻቸውን እያስመዘገቡ ይገኛሉ።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የወጣው መርሃ ግብር እንደሚያመለክተው የመራጮች ምዝገባ የካቲት 28 ቀን 2018 ዓ.ም የሚጀምር ይሆናል።

በዚህ የምርጫ ሂደት በተለይም የሲቪክ ማህበራት ግንዛቤ በመፍጠርና በታዛቢነት ጭምር በመሳተፍ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት መጎልበት የድርሻቸውን አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ይሆናል።

ከዚህ አንፃር ለዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ የሲቪክ ማህበራት ዝግጅት ምን ይመስላል? ሲል የኢዜአ ሪፖርተር በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የሚገኙ የሲቪክ ማህበራት ድርጅቶችን አነጋግሯል።

የሲቪክ ማህበራቱም ለምርጫው ሰላማዊነት፣ ዴሞክራሲያዊነት፣ አሳታፊነትና ተዓማኒነት የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አረጋግጠዋል።


 

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መምህራን ማህበር ፕሬዚዳንት መምህር አካሉ አለማየሁ፤ የምርጫ ሂደት ለአንድ ሀገር የዴሞክራሲ ስርዓትና ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።

በዚህ ረገድ በምርጫው የፓርቲዎችን ፖሊሲና ስትራቴጂ በአግባቡ በመረዳት ህዝቡ በምርጫው ጠንካራ ተሳትፎ ማድረጉ አስፈላጊ ነው።

በመሆኑም ግንዛቤ በመፍጠርና ለሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሂደት የሲቪክ ማህበራት የላቀ ሚና ይጠበቃል ያሉት ፕሬዚዳንቱ በዚሁ ልክ ለዘንድሮው ምርጫ መሳካት እየተዘጋጀን ነው ብለዋል።

መምረጥ መሰልጠን መሆኑን ጠቁመው ለዚህም በተቀመጠው የጊዜ ሰለዳ መሰረት ካርድ መውሰድ እንደሚገባና ማህበሩም በዚህ ላይ ህብረተሰቡን በመቀስቀስ በምርጫው የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግ እየተሰራ ነው ብለዋል።


 

የክልሉ ሴቶች ፌደሬሽን ስራ አስፈፃሚ እና የካፋ ዞን ሴቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አስማረች ሀይሌ በበኩላቸው፣ ሴቶች በመመረጥ፣ በመምረጥና በመታዘብ መብታቸውን በተገቢው እንዲጠቀሙ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።

የዘንድሮው ምርጫ ከዚህ ቀደም ከነበረው በተሻለ መልኩ ሰላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊ፣ ፍትሐዊና ተዓማኒ እንዲሆን የሴቶች ሚና የጎላ መሆኑን ጠቅሰው የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ግንዛቤ የማስረጽ ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።  


 

ወጣቱ በታዛቢነትና በበጎ ፈቃድ አሰልጣኝነት ስለምርጫው ለህብረተሰቡ ግንዛቤ በማስጨበጥ የተጠናከረ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን የክልሉ ወጣቶች ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንትና የካፋ ዞን አስተባባሪ ወጣት ፍሬው ደምሴ ገልጿል።

በሁሉም የምርጫ ጣቢያ በታዛቢነት የሚሳተፉ ወጣቶች ምዝገባ እየተካሄደ መሆኑን ጠቁሞ ለምርጫው ስኬት ወጣቱ ሚናውን በተሻለ መልኩ እንዲወጣ ከምርጫ ቦርድና ከሌሎች ሲቪክ ማህበራት ጋር በቅርበት እየተሰራ ነው ብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም