ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ በውሃ ሃብት ልማት ዘርፍ በተከናወኑ ተግባራት የንጹህ መጠጥ ውሃ ሽፋን ላይ ከፍተኛ ዕድገት ተመዝግቧል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 6/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ በውሃ ሃብት ልማት ዘርፍ በተከናወኑ ተግባራት የንጹህ መጠጥ ውሃ ሽፋን ላይ ከፍተኛ ዕድገት መመዝገቡን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ገለጸ።

የአፍሪካ ሕብረት 48ኛው የሥራ አስፈፃሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ትናንትና ከትናንት በስቲያ ለሁለት ቀናት በአዲስ አበባ የሕብረቱ ዋና መስሪያ ቤት ሲካሄድ ቆይቶ ተጠናቋል።

39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔም "ዘላቂ የውሃ አቅርቦትና ደህንነቱ የተጠበቀ የንጽህና አጠባበቅ ስርዓቶችን ማረጋገጥ፤ ለአጀንዳ 2063 ግቦች ስኬታማነት” በሚል መሪ ሀሳብ ነገና ከነገ በስትያ ይቀጥላል።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር አማካሪ ሞቱማ መቃሳ፤ የሕብረቱ መሪ ሃሳብ በአፍሪካ የውሃ ደኅንነትና ንጽህና አጠባበቅ ላይ ማተኮሩ ለኢትዮጵያ የልማት ስኬት ትልቅ አቅም ይሆናል ብለዋል።

የአፍሪካ ሀገራትም ደኅንነቱ የተጠበቀ አስተማማኝ የውሃ መሠረተ ልማት በመገንባት የአህጉሪቷን ዜጎች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትብብር መስራት እንደሚኖርባቸው ገልጸዋል።

በዚህ በኩልም ኢትዮጵያ የዜጎችን የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ከማሻሻል ባሻገር የጎረቤት ሀገራት ህዝቦችን ጭምር ተጠቃሚ እያደረገች መሆኗን ተናግረዋል።

የሕብረቱ መሪ ሃሳብ በአፍሪካ የውሃ ደኅንነትና ንጽህና አጠባበቅ መሪ ሃሳብም አህጉራዊ የውሃና ሳኒቴሽን ሥርዓትን ማሻሻል የሚያስችል የኢንቨስትመንት ዕድል እንደሚፈጥር አንስተዋል።

በኢትዮጵያ የውሃ ሃብትና ሳኒቴሽን ሥርዓት ለማሻሻል የተመዘገቡ ስኬቶችን ለማስቀጠልም ሰፋፊ የመሠረተ ልማት ግንባታ ሥራዎች እየተሰሩ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

በዚህም በንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ በውሃ አስተዳደርና በታዳሽ የኃይል ማመንጫ የልማት ሥራዎች ለአህጉሪቷ ጭምር አርዓያ የሚሆን ስኬት ማስመዝገቧን ገልጸዋል። 

በውሃ ሃብት የሚደረግ ኢንቨስትመንት ከፍተኛ አቅም ይጠይቃሉ ያሉት አቶ ሞቱማ፤ ኢትዮጵያም የአፍሪካ ሕብረት አጀንዳዎችን ለማሳካት ከልማት አጋሮች ጋር በመተባበር እየሰራችበት ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም