ቀጥታ፡

የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ በተሰራው ስራ ለውጥ ማምጣት ተችሏል

ነቀምቴ ፤ የካቲት 6/2018(ኢዜአ)፦ባለፉት ዓመታት በኢኮኖሚያዊ፣ በፖለቲካና በማህበራዊ መስክ የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ በተሰራው ስራ ለውጥ ማምጣት መቻሉ ተገለጸ።

በነቀምቴ ከተማ የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ ያለመ ''በሴቶች ተሳትፎ የፀናችና የበለፀገች ኢትዮጵያ'' በሚል መሪ ሀሳብ የውይይት መድረክ ተካሄዷል።

በመድረኩ ላይ የብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት ሴቶች ክንፍ የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ ወይዘሮ አሰለፈች ታደሰ እንደገለጹት፣ ባለፉት ዓመታት የሴቶች ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት በሁሉም መስክ ውጤት እያሳየ ነው።


 

ፓርቲው የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ፣ ወደ አመራር እንዲመጡ ለማገዝ፣ በገቢ ራሳቸውን እንዲችሉ እና የኑሮ ደረጃቸውን ለማሻሻል አበክሮ ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል።

እስካሁን የተገኘውን ውጤት ለማስቀጠል የሴቶች ሚና ከፍተኛ መሆኑን አንስተው የሰላም እና የልማት እንቅስቃሴውን በማፋጠን ረገድ የሴቶች ተሳትፎ ይጠናከራል ብለዋል።

በተለይ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ፣ አሳታፊ፣ ፍትሃዊ እና ሰላማዊ እንዲሆን የድርሻቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው አስረድተዋል።

በብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የሴቶች ክንፍ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ አያንቱ ይሻው በበኩላቸው፤ ሴቶች የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታን በማጠናከር ረገድ ትልቅ ሚና አላቸው ብለዋል።


 

በክልሉ በሁሉም ዘርፍ የተጀመሩ ስራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል የሴቶች ተሳትፎን የማሳደግ ተግባር በትኩረት እየተከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል።

መጪው ጠቅላላ ምርጫ ስኬታማ እንዲሆን በተለይ የሴቶች አደረጃጀቶች ከወዲሁ አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረጉ ነው ብለዋል።

በዞኑ የሴቶችን ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚያስችሉ ስራዎች በትኩረት እየተከናወኑ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በብልጽግና ፓርቲ የምስራቅ ወለጋ ዞን ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ በጂ ሞሲሳ ናቸው።

በግብርና፣ በንግድ እና በትምህርት የሴቶችን ተሳትፎ በማሳደግም ራሳቸውን ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲያደርሱ ይሰራል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም