ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የግብርና ምርታማነት ስኬቶች የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ ረገድ በአርዓያነት የሚወሰዱ ናቸው 

አዲስ አበባ፤ የካቲት 6/2018(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የተገኙ ስኬቶች በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት በአርዓያነት ሊወሰዱ የሚችሉ መሆናቸውን በአፍሪካ የአረንጓዴ አብዮት ህብረት (AGRA) የሽርክና እና የንግድ ልማት ኃላፊ ካሲ ካርል ማንላን ገለጹ።  

የአፍሪካ ሕብረት 48ኛው የሥራ አስፈፃሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ በአዲስ አበባ ለሁለት ቀናት ሲካሄድ ቆይቶ ትናንት ተጠናቋል።

39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔም "ዘላቂ የውሃ አቅርቦትና ደህንነቱ የተጠበቀ የንጽህና አጠባበቅ ስርዓቶችን ማረጋገጥ፤ ለአጀንዳ 2063 ግቦች ስኬታማነት” በሚል መሪ ሀሳብ ነገና ከነገ በስትያ በአዲስ አበባ ይካሄዳል።

በአፍሪካ የአረንጓዴ አብዮት ሕብረት (AGRA) የሽርክና እና የንግድ ልማት ኃላፊ ካሲ ካርል ማንላን፤ የውሃ ሃብት ልማትና ንፅህና አጠባበቅ ለማህበረሰብ ጤና ወሳኝ ጉዳዮች ናቸው ብለዋል።

በዚህም በአፍሪካ የግብርና ምርታማነትን በማረጋገጥ የዜጎችን የምግብ ሉዓላዊነት እውን ለማድረግ የውሃ ሃብት ልማትና የመስኖ መሰረተ ልማቶችን ማስፋፋት እንደሚገባ ጠቁመዋል። 

በውሃ ሃብት ልማት የአህጉሪቷን የግብርና ምርቶች በብዛትና በጥራት የማምረት አቅም በመፍጠር የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ እንደሚገባ አንስተዋል።

በዚህም የአፍሪካ ሀገራት የሀገር ውስጥ ምርታማነትን በማሳደግ የአህጉሪቷ ዜጎች ጤናማና አስተማማኝ የአመጋገብ ሥርዓት የሚያገኙበትን ምኅዳር መፍጠር እንደሚኖርባቸውም አስገንዝበዋል።

በዚህ ረገድ በኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ ናቸው ያሉት ኃላፊው፤ የኢትዮጵያ የግብርና ምርታማነት ስኬቶችም ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ትምህርት የሚሆኑ ናቸው ብለዋል። 

የኢትዮጵያ የግብርና ምርታማነት ሥርዓቶችም የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ አስደናቂ ሥራዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም