ቀጥታ፡

በስፔን ጥሎ ማለፍ የግማሽ ፍጻሜ የመጀመሪያ ጨዋታ አትሌቲኮ ማድሪድ ባርሴሎናን በሰፊ የግብ ልዩነት አሸነፈ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 5/2018 (ኢዜአ)፦ በስፔን ጥሎ ማለፍ (ኮፓ ዴል ሬይ) የግማሽ ፍጻሜ የመጀመሪያ ጨዋታ አትሌቲኮ ማድሪድ ባርሴሎናን 4 ለ 0 ረቷል።

ማምሻውን በዋንዳ ሜትሮፖሊታኖ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ አንቶዋን ግሪዝማን፣ ጁሊያን አልቫሬዝ፣ አዲስ ፈራሚው አዴሞላ ሉክማን እና የባርሴሎናው ግብ ጠባቂ ኤሪክ ጋርሺያ በራሱ ላይ የማሸነፊያ ግቦቹን አስቆጥረዋል።

በመጀመሪያው አጋማሽ ፍጹም የጨዋታ ብልጫ የወሰደው አትሌቲኮ ማድሪድ በ45 ደቂቃ አራት ግቦችን አስቆጥሯል።

የባርሴሎናው ተከላካይ ኤሪክ ጋርሺያ በ86ኛው ደቂቃ በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል።

ባርሴሎና በሁለተኛው አጋማሽ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ቢሞክርም አትሌቲኮ ማድሪድ ውጤቱን ማስጠበቅ ችሏል።

አትሌቲኮ ማድሪድ ወደ ፍጻሜ የማለፍ እድሉን አስፍቷል።

አስደንጋጭ ሽንፈት ያስተናገደው ባርሴሎና ውጤቱን የመቀልበስ ከባድ ፈተና በመልሱ ጨዋታ ይጠብቀዋል።

የመልሱ ጨዋታ የካቲት 24 ቀን 2018 ዓ.ም በካምፕ ኑ ስታዲየም ይደረጋል።

ትናንት በተደረገው ሌላኛው የስፔን ጥሎ ማለፍ ዋንጫ የግማሽ ፍጻሜ የመጀመሪያ ጨዋታ ሪያል ሶሳዬዳድ ከሜዳው ውጪ አትሌቲኮ ቢልባኦን 1 ለ 0 አሸንፏል።

የመልሱ ጨዋታ የካቲት 25 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳል።

ባርሴሎና የወቅቱ የውድድሩ አሸናፊ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም