አርሰናል ከብሬንትፎርድ ጋር አቻ ተለያየ - ኢዜአ አማርኛ
አርሰናል ከብሬንትፎርድ ጋር አቻ ተለያየ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 5/2018 (ኢዜአ)፦ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የ26ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ብሬንትፎርድ እና አርሰናል ያደረጉት ጨዋታ አንድ አቻ አጠናቋል።
ማምሻውን በጂቴክ ኮምዩኒቲ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ኖኒ ማኑዌኬ በ61ኛው ደቂቃ በግሩም ሁኔታ በግንባሩ በመግጨት ያስቆጠረው ግብ መድፈኞቹን መሪ አድርጓል።
በ71ኛው ደቂቃ ከረጅም እጅ ውርወራ የተገኘውን ኳስ ኪን ሉዊስ-ፖተር በግንባሩ ገጭቶ ከመረብ ላይ ባሳረፋት ጎል ብሬንትፎርድ አቻ ሆኗል።
ብሬንትፎርድ በሊጉ ከእጅ ውርወራ አራተኛ ግቡን ማስቆጠር ችሏል።
በጨዋታው አርሰናል ከብሬንትፎርድ ጠንካራ ፉክክር ገጥሞታል።
ሁለተኛው አጋማሽ የተሻለ እንቅስቃሴ የተደረገበት ሲሆን ሁለቱም ቡድኖች ጨዋታውን የማሸነፍ እድላቸውን መጠቀም አልቻሉም።
በዋንጫ ፉክክሩ ወሳኝ ነጥብ የጣለው የሊጉ መሪ አርሰናል ነጥቡን ወደ 57 ከፍ አድርጓል።
ከተከታዩ ማንችስተር ሲቲ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ከስድስት ወደ አራት ዝቅ ብሏል።
ብሬንትፎርድ በ40 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃን ይዟል። ቡድኑ ባለፉት ሶስት ጨዋታዎች አልተሸነፈም።