የክልሉን የልማት አቅም በመጠቀም የመሰረተ ልማት ችግሮችን ደረጃ በደረጃ በመፍታት ለህዝብ ጥያቄ ምላሽ እየተሰጠ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የክልሉን የልማት አቅም በመጠቀም የመሰረተ ልማት ችግሮችን ደረጃ በደረጃ በመፍታት ለህዝብ ጥያቄ ምላሽ እየተሰጠ ነው
ታርጫ፤ የካቲት 5/2018(ኢዜአ)፦የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልልን የልማት አቅም በመጠቀም የመሰረተ ልማት ችግሮችን ደረጃ በደረጃ በመፍታት ለህዝብ ጥያቄ ምላሽ እየተሰጠ ነው ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ገለፁ።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 9ኛ መደበኛ ጉባኤውን በታርጫ ከተማ እያካሄደ ይገኛል።
በዛሬው ውሎው የምክር ቤት አባላቱ በልማት፣ በሰላምና በመልካም አስተዳደር ዘርፎች በተደረገ ሰፊ ጥረት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ ተግባራት መከናወናቸውን አንስተዋል።
በተለይም ያደሩና የቆዩ የውሃ፣ የድልድይ፣ የመንገድና ሌሎች የመሰረተ ልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ የተደረገው ሰፊ ርብርብ የሚበረታታና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት መሆኑንም ገልፀዋል።
የክልሉ መንግስት የመሰረተ ልማት ችግሮችን ለመፍታት ያከናወናቸው ተግባራት የሚበረታቱ መሆኑን አባላቱ ጠቅሰው የገጠር ተደራሽ መንገዶችና ድልድዮች ግንባታ ላይ ትኩረት እንዲደረግም ጠይቀዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ ፤ ክልሉ ያለውን አቅም በመጠቀም ቅድሚያ የሚሰጣቸውን የመሰረተ ልማት ችግሮች ደረጃ በደረጃ በመፍታት ለህዝብ ጥያቄ ምላሽ እየተሰጠ ነው ብለዋል።
ለዚህም በመንገድና ድልድይ መሰረተ ልማት ግንባታ ሂደት ውስጥ የማህበረሰቡ ተሳትፎና ድርሻ ትልቅ አቅም መሆኑን አንስተው ይህም ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።
ግንባታቸው በፌደራል መንግስት እየተከናወኑ የሚገኙ የአስፋልት መንገዶች እንዲፋጠኑ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅርበት እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።
በግብርናው ዘርፍም የምርጥ ዘር አቅርቦትን በማሻሻል ውጤታማ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፣ የህብረት ስራ ማህበራትን አቅም የማጠናከር ስራም ትኩረት እንደሚሰጠው ጠቁመዋል።
በክልሉ ከኮሪደር ልማት ጋር በማያያዝ ዘመናዊ ከተሞችን ለመፍጠር በሰፊው እየተሰራ መሆኑን አመልክተው መሰረተ ልማትን በማሟላትና በማስተር ፕላን የሚመሩ ከተሞችን እውን ከማድረግ አኳያ ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።
ከማዘጋጃ ቤት፣ ከንግድና ከገቢ ጋር የሚገናኙ አገልግሎቶችን ዲጂታላይዝ በማድረግ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት የመሶብ የአንድ ማእከል አገልግሎትን ለማስፋት የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።