ቀጥታ፡

በሀገሪቱ የቡና ምርት ጥራት ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ የቅምሻ ባለሙያዎችን ማፍራት ላይ ትኩረት ተደርጓል

ሀዋሳ ፤ የካቲት 5/2018(ኢዜአ)፦በሀገሪቱ የቡና ምርት ጥራት ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ የቅምሻ ባለሙያዎችን ማፍራት ላይ ትኩረት መደረጉን የኢትዮጵያ ምርት ገበያ አስታወቀ።

ምርት ገበያው ዘመናዊና ጥራት ላይ ያተኮረ ግብይትን ለማሳለጥ ያለመ የሰው ኃይል ለማፍራት አካዳሚ ከፍቶ እየሰራ ነው።

ዛሬ በሀዋሳ ማዕከል የተጀመረው የመጀመሪያ ዙር ስልጠናም የቡና ቅምሻ ደረጃ አወጣጥ ላይ ማተኮሩ ተመልክቷል።

የምርት ገበያው አካዳሚ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ተሾመ፤ ምርት ገበያው ቡናን ጨምሮ የግብርና ምርቶች ግብይትን በማዘመን ጥራታቸውን እንዲጠብቁ ለማድረግ ለክህሎት ስልጠና ትኩረት በመስጠት እየሰራ ነው ብለዋል።

በዚህም የቡና መገኛ የሆነችው ኢትዮጵያ የሚገባትን ለማግኘት፣ በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪነቷን ለማጠናከርና የምርት ሂደቱ የጥራት ደረጃውን እንዲጠብቅ ለማድረግ በዕውቀት የሚሰራ የሰው ኃይል ለማፍራት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።

የዓለም አቀፍ ገበያው የሚፈልገውን የጥራት ደረጃ የሚመጥን ምርት ለማውጣትና በድህረ ምርት ሂደት ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመቅረፍ በክህሎት የዳበረ የሰው ሀይል  ማብቃት አስፈላጊ መሆኑን አመልክተዋል።


 

መሰል ስልጠና በአዲስ አበባ ማእከል ከተጀመረ ሶስት ዓመታት እንዳስቆጠረ ገልፀው በዚህም 480 ባለሙያዎች መሰልጠናቸውንና ስልጠናውን በማስፋት ዛሬ በሀዋሳ መጀመሩንም ጠቁመዋል።

ሀገሪቱ ከወጭ ንግድ የሚገባትን እንድታገኝ በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ሀይል ማፍራት እንደሚገባ የገለጹት ደግሞ  በምርት ገበያው የሀዋሳ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅና የቡና ጥራት ባለሙያ አቶ ነቢያት ጀማል ናቸው። 

የሀዋሳ ስልጠና ማዕከልም በመጀመሪያው ዙር 27 ሰልጣኞችን ተቀብሎ በቡና ምርት ጥራት ማስጠበቅ ላይ የክህሎት ስልጠና እየሰጠ ነው ብለዋል።

ከሰልጣኞች መካከል ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን ሀምበላዋመና ወረዳ የመጡት አቶ ድልነሣ አያልነህ፤ በቡና ልማት ዘርፍ ልምዱ ያላቸው ቢሆንም ከጥራት አንጻር የሚነሳውን ችግር ለመፍታት በስልጠናው እየተሳተፉ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በተለይም በምናመርተው ልክ ተጠቃሚ ለመሆን የዓለም አቀፍ ገበያው የሚፈለገውን ጥራት ደረጃ ማሟላት ይገባል ያሉት ሰልጣኙ ለዚህ ደግሞ የምርት ገበያው የጀመረው ስልጠና ክህሎታቸውን በማዳበር እንደሚያግዛቸው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም